የማርበርግ ቫይረስ (Marburg Virus Disease)

የማርበርግ ቫይረስ ተላላፊ የሆነ የንዳድ በሽታ ነው። ዝርያውም ፊሎቫይረስ በመባል የሚመደብ ሲሆን ከኢቦላ ቫይረስ ጋር ይቀራረባል።


ዛሬ ህዳር 5፣ 2018 ዓም በኢትዮጵያ የተወሰኑ ሰዎችን ያጠቃ በቫይረስ የሚመጣ አደገኛ ትኩሳት ወምፍሳስ ደም (Viral Hemorrhagic Fever) ወረርሽኝ መንስኤው የማርበርግ ቫይረስ መሆኑን አረጋግጧል።


ይህ ትምህርታዊ ጽሁፍ ስለማርበርግ ቫይረስ ምንነት፣ ሥርጭት ፣ ምልክቶች ፣ ህክምና እና የመከላከል መንገዶች ዙሪያ በማተኮር ያብራራል።


የቫይረሱ ምንነት

  • ዝርያ፤ ፊሎቫይረስ (filoviruses)
  • የቫይረሱ ሽፋን እና ዘረመል፤ በቅባታም ኢንቨሎፕ (ሽፋን) የተጠቀለለ ሲሆን ጄኔቲክ ስሪቱ አር ኤን ኤ ነው።
  • ተፈጥሮዊ ምቹጌ፤ ቫይረሱ የሚኖረው በሌሊት ወፎች ነው። የሌሊት ወፎች ላይ በሽታ አምጭ አይደለም።
  • አንዴ ወደሰው ከተላለፈ ግን በሽታ ያመጣል።
  • ከሰው ወደ ሰውም ይተላለፋል።

የማርበርግ ቫይረስ እንዴት ይተላለፋል?

የማርበርግ ቫይረስ ስርጭት የሚጀምረው በቫይረሱ ከተያዙ የሌሊት ወፎች እና አካባቢያቸው ወደ ሰው ሲተላለፍ ነው። የሌሊት ወፍ በሚገኙበት ዋሻ ውስጥ የማእድን ቁፋሮ ስራ የሚሰሩ ስዎች፣ ጎብኝዎች ለቫይረሱ ሊጋለጡ ይችላሉ። በሌሊት ወፍ ሽንት፣ ኩስ እና ምራቅ የተበከሉ ነገሮችም ቫይረሱን ሊያስተላልፉ ይችላሉ። ዋና የቫይረሱ ምቹጌ የሌሊት ወፍ ቢሆንም ዝንጀሮዎች እና አሳማዎችም አንዳንዴ ጊዜያዊ የቫይረሱ መሸጋገሪያ ሊሆኑ ይችላሉ የሚሉ ጥናቶች አሉ።


ቫይረሱ አንዴ ሰው ጋር ከደረሰ በኋላ ከሰው ወደ ሰው ይተላለፋል። ቫይረሱ የሚዛመተው ከታመመ ሰው ደም እና የሰውነት ፈሳሽ (ትውከት፣ ሰገራ፣ ሽንት፣ ምራቅ፣ ላብ፣ የጡት ወተት፣ የብልት ፈሳሽ ወዘተ) ጋር በቀጥታ ንክኪ ነው። በቫይረሱ የተያዘ ሰው የተጠቀመባቸውን መርፌ፣ ቁሳቁሶች፣ የተነካኩ ልብሶች ወዘተ ቫይረሱን ያስተላልፋሉ። በግብረ ስጋ ግንኙነትም ይተላለፋል። አስከሬንም መንካት ቫይረሱን ያስተላልፋል።


የማርበርግ ቫይረስ ህመም ምልክቶች ምንድን ናቸው?

ቫይረሱ ወደሰውነታችን ከገባ በኋላ የሰውነት የበሽታ ተከላካይ ህዋሶችን በማጥቃት በፍጥነት ይራባል፣ ይሰራጫል። በቫይረሱ የተጠቁ የየበሽታ ተከላካይ ህዋሶቻችን ከፍተኛ መጠን ያላቸውን ኬሚካሎች ይለቃሉ። የሰውነታችንን ጸረ-ቫይረስ ምላሽ ከቁጥጥር ውጭ በመቀሰቀስ (massive inflammatory response, cytokine storm) መላ የደም ስርን እንዲቆጣ በማድረግ ሰውነትን ይጎዳል። በዚህ ሂደት የበሽታ ተከላካይ ህዋሶቻችን ስለሚጎዱ የበሽታ መከላከያ አቅማችን ይዳከማል።


በቫይረሱ የተያዘ ሰው ምንም የበሽታው ምልክት ሳያሳይ ከጥቂት ቀናት እስከ ሶስት ሳምንታት ሊቆይ ይችላል።


የማርበርግ ቫይረስ ህመም የመጀመሪያ ምልክቶች እንደሌሎች ቫይረሶች ሁሉ ጉንፋን መሰል እንደ ከፍተኛ ትኩሳት፣ ራስ ምታት፣ ጉሮሮ መቁሰል፣ የጡንቻና የመገጣጠሚያ ህመም እና ድካም ናቸው። እነዚህ የመጀመሪያ የቫይረሱ ምልክቶች ከሌሎች በርካታ አጣዳፊ ትኩሳት አምጭ ተላላፊ በሽታዎች ጋር ሊመሳሰሉ ይችላሉ። ለምሳሌ የወባ ህመም (ማንቀጥቀጥ የሚበረታ ሲሆን በቀላሉ የወባ ምርመራ በማድረግ ይለያል)፣ ታይፎይድ (የትኩሳቱ አጨማመር ለዬት ያለ ጸባይ አለው፣ የተበከለ ምግብ / መጠጥ መጋለጥ አጋጣሚ ይኖራል)፣ የማንጅራት ገትር ህመም፣ ኮቪድ-19 ወዘተ ተቀራራቢ ምልክቶች ሊኖራቸው ይችላል።


እነዚህ ምልክቶች ከታዩ ከጥቂት ቀናት በኋላ ጠንከር ያለ ማቅለሽለሽ፣ ማስታወክ፣ ተቅማጥ እና የሆድ ህመም የመሳሰሉ የጨጓራና አንጀት ህመም ምልክቶች ያሳያሉ።


በመቀጠል በሽታው እየገፋ ከባድ ምልክቶች ይመጣሉ። በቆዳ ላይ፣ አፍና አፍንጫ ወይም የውስጥ የአካል ክፍል ላይ ደም መፍሰስ ያመጣል። ህመሙ እየጸና ሲሄድ የደም ግፊት ከልክ በታች መቀነስ፣ የጉበት፣ ኩላሊት እና ሌሎችም የሰውነት ክፍሎቻችን ይጎዳሉ። ሲብስ የብዝሃ-አካል መድካም ያመጣል። ገዳይነታቸው ከዚህ ጋር የተያያዘ ነው።


በማርበርግ የተያዘ ሰው የሞት ምጣኔ በአማካይ ወደ 50% ገደማ ይደርሳል። እንደ የቫይረስ ዝርያ፣ የወረርሽኝ ምላሽ ውጤታማነት እና የህክምና አገልግሎት ተደራሽነት ላይ ተመስርቶ ይህ የሞት ምጣኔ ዝቅ ወይም ከፍ ሊል ይችላል። ለምሳሌ ጠንካራ የወረርሽን ቁጥጥር ያደረገችው ሩዋንዳ የሞት ምጣኔስ ወደ23 በመቶ አካባቢ ዝቅ ያለ ነበር። ይህ የሩዋንዳን የጤና ስርአት ጥንካሬ ማሳያ ተደርጎ ሲመሰገን ነበር። ወረርሽኙ እንደተሰማ ከፍተኛ ገንዘብ በመመደብ የባለሙያ፣ የሙከራ መድሃኒት እና የህክምና ግብአቶች በወቅቱ ምላሽ ስለተሰጠ ሩዋንዳ በማርበርግ ቁጥጥር ሌሁላችንም አስተማሪ የሆነ ድንቅ ስራ ሰርታለች።  


ከቫይረሱ የተረፉ ሰዎች ሙሉ ለሙሉ ለማገገም ከቀናት እስከ ሳምንታት ሊወስድባቸው ይችላል። በተለይም ድካም፣ ቁርጥማት እና የስነ ልቦና ጫና የተራዘሙ ሊሆኑ ይችላሉ።


የማርበርግ ቫይረስ ምርመራዎች

አጠቃላይ የደም ምርመራ ላይ አማላካች የሆኑ የላብራቶሪ ውጤቶች ሊኖሩ ይችላሉ ለምሳሌ የደም ህዋሳት ቁጥር መቀነስ፣ የጉበት ምርመራ ኖርማል አለመሆን፣ የኩላሊት ጉዳት ምልክት መኖር ወዘተ ሊገኝ ይችላል።


የቫይረስ ህመሙን ለማረጋገጥ የማረጋገጫ ምርመራ ያስፈልጋል። የቫይረሱን ዘረመል የሚለዩ ፕ ሲ አር ሞለኩዩላር ምርመራዎች፣ አንቲጂን ምርመራዎች፣ አንቲቦዲዎችን ያካትታሉ። የታካሚ ናሙናዎች እጅግ በጣም አደገኛ ስለሆኑ እነዚህ ምርመራዎች የሚከናወኑት በብሔራዊ የባዮሴፍቲ ፕሮቶኮሎች መሠረት በልዩ ላቦራቶሪ ማእከሎች ውስጥ ብቻ ነው።


ማርበርግ ህክምና አለው?

ህክምናው በአብዛኛው የሚያካትተው የሰውነት ፈሳሽ በግሉኮስ መተካት፣ በባለሙያ ክትትል ማድረግ እና ተጓዳኝ ችግሮችን ማከም ላይ ያተኩራል። እንዳስፈላጊነቱ የትኩሳት ማብረጃ እና የህመም ማስታገሻ መስጠት ይገባል። በጣም ደም መፍሰስ ላጋጠማቸው የደም ልገሳ ሊፈልጉ ይችላሉ።


ከእነዚህ የህክምና ድጋፎች ባሻገር የሚሰጡ የጸረ-ቫይረስ ህክምናዎች የሉም። እስካሁን ለማርበርግ የተረጋገጠ እና ፍቃድ ያገኘ  ጸረ-ቫይረስ መድሃኒት የለም። በጥናትና ምርምር ደረጃ ለኮቪድ ይውል የነበረ ሬምዴዜቪር የሚባል መድሃኒት እየተሞከረ ይገኛል።


እስካሁን ፍቃድ ያለው የማርበርግ ክትባትም አልተገኘለትም። በምርምር ደረጃ ያሉ ጥቂት እጩ የማርበርግ ክትባቶች ጥናት እየተሰራባቸው እና እየበለጸጉ እንደሚገኝ የሚጠቅሱ መረጃዎች አሉ።


በሽታውን እንዴት መከላከል እንችላለን?

በሽታው እንዳይዛመት ዋና መከላከያ መንገዱ በቫይረሱ የተጠረጠረን ሰው መለየትና ኳራንቲን ማድረግ ነው። በበሽታው ከተያዙ ግለሰብ የሰውነት ፈሳሾች ጋር ንክኪን ማስወገድ ይገባል። የታመመን ሰው በቤት ለማከም ከመሞከር ይልቅ ወዲያዉኑ ወደጤና ተቋም ሄዶ እንዲታከም ማድረግ የተሻለ ነው። እያንዳንዱ ሰው እጁን በአልኮል ወይም በሳሙና በደንብ በመታጠብ ንጽህና መጠበቅ አለበት። ከታማሚ ሰው ጋር ንክኪ ያላቸውን አልባሳት፣ እቃዎችና እና ምንጣፎችን በክሎሪን በረኪና ዘፍዝፎ ማጽዳት ይገባል።


ከአስተላልፊ የሌሊት ወፍ መኖርያ ዋሻዎችና ጎሬዎች አይግቡ። በተለይ ጂኦሎጅስቶች፣ የማእድን ቁፋሮ ሰራተኞች አስፈላጊዉን የመከላከያ መንገድ ማድረግ ይኖርባቸዋል። የሌሊት ወፍ በጭራሽ መንካት ወይም መጠጋት የለብንም። ወረርሽኝ በተከሰተበት አካባቢ ሁሉንም የእንስሣት ተዋጽኦ ምግቦች በደንብ አጥቦ እና አብስሎ መመገብ ይገባል።


በጤና ተቋማትም ከመደበኛ ጥንቃቄዎች ባሻገር የኢንፌክሽን መከላከያ እርምጃዎች ካልተተገበሩ የጤና ባለሙያዎች ለከፍተኛ አደጋ ይጋለጣሉ። የተሳለጠ የቅድመ ልየታ ስርአት መዘርጋት ይፈልጋል።  ከጓንት እና ማስክ በተጨማሪ አይን እና ፊት መከላከያ ማድረግ ያስፈልጋል። የተለያዩ ኤሮሶል ብናኞችን የሚፈጥሩ የህክምና ፕሮሲጀሮች ሲሰሩ የአየር ወለድ ጥንቃቄዎች (ለአብነትም N95 ማስክ)  መተግበር አለባቸው። የመርፌ እና ሌሎች ቆሻሻ አወጋገድም ጥንቃቄ ይፈልጋል።


በማህበረሰብ ውስጥ ደህንነቱ የተጠበቀ የቀብር ሥነ ሥርዓቶች መተግበር አለባቸው። በበሽታው ምክንያት የሞተ ሰውን አስከሬን አለመንካት። በባለሙያ በሚገባ በአስከሬን መጠቅለያ እንዲሸፈን በማድረግ ወዲያውኑ በባለሙያ መቅበር ይመከራል።


የማርበርግ ቫይረስ ምን ያህል አሳሳቢ ነው?

ማርበርግ ቫይረስ ገዳይነቱ ከኮሮና ቫይረስ ጋር ሲወዳደር በጣም ከፍተኛ ቢሆንም ቅሉ በጠንካራ የመከላከል እርምጃዎች መቆጣጠር የሚቻል ህመም ነው።


የሚተላለፈው ከሰውነት ፈሳሾች ጋር በቅርበት በመነካካት እንጂ በገበያ፣ በአውቶብስ ወይም በመንገድ ላይ በቅጽበታዊ አልፎ ሂያጅ ግንኙነት አይደለም።


አሁናዊ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከሆነ ማርበርግ እንደኮሮና ወይም ጉንፋን በቀጥታ በትንፋሽ አይተላለፍም። ማርበርግ አየር ወለድ ተላላፊ አይደለም። ለምሳሌ አንድ ማርበርግ የያዘው ሰው ቤት ውስጥ ወይም መኪና ውስጥ ቢያስል ማርበርግ አያስተላልፍም። ነገር ግን ታማሚው ሲያስል የሚፈናጠሩ ጥቃቅን የምራቅ ነጠብጣቦች በቀጥታ አፋችን፣ አፍንጫችን ወይም አይናችን ላይ ካረፈ ሊያስተላልፍ ይችላል። እነዚህ ብናኝ ነጠብጣቦች ያረፉበትን ነገር በእጃችን ነክተንም ከሆነ ማርበርግ ሊይዘን ይችላል።


የማርበርግ ተዛማችነት (transmission rate, Ro) መጠነኛ ነው። ለማነጻጸር ያህል በቅርቡ ከነበረው ኮቪድ ቫይረስ ጋር እንኳ ብናወዳድረው የኮቪድ የመዛመት / የስርጭት ምጣኔው ከሁለት እስከ ሶስት እጥፍ ከማርበርግ ይበልጣል። ይህ ማለት አንድ በማርበርግ የተያዘ ሰው በአማካኝ ሌሎች ስንት ሰዎችን ሊበክል ይችላል ተብሎ ሲሰላ ትንሽ ነው ማለት ነው። ሌላው የቫይረሱ ጥሩ ጎኑ ደግሞ አንድ በማርበርግ የተያዘ ሰው ቶሎ አስተላላፊ አይሆንም። ኡደቱ ቀርፋፋ ነው።


ይህ ተዛማችነቱን ይገታዋል። ስለዚህ በጠንካራ የጤና ቁጥጥር ስርአት ስርጭቱን በቶሎ ማንቁርቱን ይዘን ልናስቆመው እንችላለን ማለት ነው። እንደኮቪድ አገር ምድሩን የሚያዳርስ አይነት ወረርሽኝ አይደለም።


ማጠቃለያ መልእክት

የማርበርግ ቫይረስ አስፈላጊው እርምጃ በፍጥነት እና በተቀናጀ ሁኔታ ካልተደርገ ሞት እንደሚያስከትል ጥርጥር የለዉም። እያንዳንዱ ሰው የመከላከያ እርምጃዎችን ከተገበረ፣ የታመሙት በጊዜ ተለይተው ከታከሙ በቀላሉ ልንቆጣጠረው የምንችል ደካማ ቫይረስ ነው።


ኢትዮጵያዊ ተመራማሪዎችም መድሃኒቶች እና ክትባቶች ላይ ጥልቅ ምርምር በማድረግ ህዝባችንን መታደግ፣ የህክምና ሳይንስን ማሳደግ ይጠበቅብናል። በዚህ ወረርሽኝ ቁጥጥር ውስጥ በምናደርገው ተጋድሎ ቫይረሱን ጨርሶ የሚያርቅ መፍትሄ ለአለም ልናበረክት እንችላለን። ቡናን፣ የባህል ህክምናን የፈጠርን ህዝቦች ምን ይሳነናል?!


ተጨማሪ መረጃዎችን ወደ 8335 እና 952 በመደዎል ማግኘት ይችላሉ። 


ማስታወሻ፦ በዚህ መጣጥፍ ላይ የተካተቱት ሀሳቦች ለአጠቃላይ መረጃ ብቻ ናቸው። ለግል ምርመራ ወይም ህክምና ዶ/ር መላኩ ጋር በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የስኳር ህክምና ክፍል መመካከር ይችላሉ።


በመረጃ የተደገፉና የተረጋገጡ ተግባራዊ የጤና ምክሮችን በዶ/ር መላኩ  Blog, Telegram, YouTube & Tiktok ይከታተሉ።

ጥያቄ፣ እርምት ወይም ግብረ መልስ ካለዎት በዚህ አድራሻ ሊንክ ይጻፉልኝ።

ይህን መረጃ ጠቃሚ ሆኖ ካገኙት ለሌሎች ያጋሩ።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top