ዘር፣ ቀለም፣ ባህል፣ ሃይማኖት ሳይገድበው በሁሉም የዓለም ጥግ ሁሉ የሚታወቅ መጠጥ በዓይነ ሕሊናህ ለመሳል ሞክር። አንዱ ኮካ ኮላ እንደሆነ ጥርጥር የለኝም። ከውሃ፣ ሻይና ቡና ቀጥሎ በአያሌው የሚጠጣ አለማቀፋዊ መጠጥ ኮካ ነው። ኮካ ከመጠጥ በላይ ኢኮኖሚያዊ ፈጠራም ነው።
በሁሉም አለማት ንፍቀ ክበብ ወደሁለት ቢሊዮን የሚጠጋ ኮካ መጠጥ በየቀኑ ይጨለጣል። የኮካን ቀይ እና ነጭ አርማ አይቶ የማይለይ የአዳም ፍጥረት የለም። የኮካ ውልደትና እድገት ግን እንዲህ እንዳሁኑ ገናና አልነበረም። በአሜሪካዋ ጆርጂያ ግዛት የአትላንታ ትንሽየ ከተማ በጥንጥዬ ፋርማሲ ውስጥ ነው የተጠነሰሰችው። አስተዋይ አእምሮ የነበረው ፔምበርተን የሚባል ፋርማሲስት ነው ቀምሞ እንዲህ በጣም ታዋቂ ለስላሳ መጠጥ እንድትሆን ያበቃት።
የኮካ ኮላ ታሪክ የማወቅ ጉጉት የወለደው የፋርማሲስቱ ጆን ስቲዝ ፔምበርተን (John Stith Pemberton) ፈጠራ እና የነጋዴው አይሳ ግሪክስ ካንድለር (Asa Griggs Candler) ስትራቴጂክ የቢዝነስ ጥበብ ድምር ዉጤት ነው።
የቡና መገኛ የሆነችው ኢትዮጵያ፣ የተትረፈረፈ ልዩ የእጽዋት ዝርያዎች መፈጠሪያ የሆነችው ኢትዮጵያ፣ አገር በቀል መጠጦች በየጓዳው የሚቀዱባት ኢትዮጵያ እንደኮካ አለምን የሚያጥለቀልቅ አዲስ መጠጥ/ምግብ/መድሃኒት ለመፍጠር አቅም እንዳለን ለማሳየት ይረዳ ዘንድ የኮካ ኮላን አስተማሪ የሆነ ጉዞ እንመርምር።
ጆን ስቲዝ ፔምበርተን፡ ኮካን የፈጠረ ፋርማሲስት!
ፔምበርተን ቀማሚ እና ተመራማሪ ፋርማሲስት ነው። በአካባቢው የሚያያቸውን ችግሮች ለመፍታት የሚረዱ መፍትሄዎችን ለመፍጠር ከፍተኛ ፍላጎት ነበረው። በጊዜው ከአሜሪካ የእርስ በእርስ ጦርነት ማብቂያ በኋላ ለህመም ማስታገሻነት በሰፊው ጥቅም ላይ የሚውለው ሞርፊን የተባለ ማስታገሻ ለአደገኛ ሱስ አጋላጭ ሆኖ አሳሳቢ ቀውስ እያመጣ ስለነበር ይህን የሚተካ ሱስ የማያስይዝ፣ አልኮል የሌለው ህመም ማስታገሻ ፍለጋ ላይ ተጠምዶ ነበር።
በዚህ እልህ አስጨራሽ ምርምር እና ቅመማ ልፋት ውስጥ እኤአ በ1886 በትንሽዬ ፋርማሲ ውስጥ ከተለያዩ ቅጠላ ቅጠሎች በተለይም የኮካ ቅጠል እና ኮላ ቅጠልን አደባልቆ አንድ ልዩ ውህድ አዘጋጀ። ይህ አዲስ መጠጥ ልዩ የሆነ ጣዕም አመጣ። ሲጠጣም ደስታ እና እርካታ ይፈጥር ነበር። ለራስ ህመም እና ድካም ማስታገሻነት የሚያገለግል ወሳኝ ፈውስ ለሰፈሩ ሰዉ ሁሉ ኮካን በብርሌ አምስት ሳንቲም መሸጥ ጀመረ።
ፔምበርተን የነጋዴነት ልምድ ስላልነበረው በመዳፉ በፈጠራት ኮካ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ማግኘት ሳይችል ፓተንቱን በትንሽ ዲናር አሳልፎ ሰጥቷል። እንዲህ ብዙዎችን ቢሊዮነር ያደረገ ምርት ፈጥሮ ለራሱ ሳይጠቀም ህይወቱን ሳይቀይር በድህነትና ደዌ አልፏል። የኮካን ድብልቅ የወደፊት ትልቅ አቅም የተረዳው አስተዋይ የቢዝነስ ሰው ካንደለር ኮካን በ2300 ብር ብቻ ሙሉ ፎርሙላውን እና ፓተንቱን ገዝቶ የግሉ አድርጎ ከጠቀለለ በኋላ ወደር የለሽ የሆነ ሃብት አካብቶበታል። ከአትላንታ አንስቶ ወደ ዓለም አቀፋዊ ኢምፓየርነት አሳድጎታል።
የካልዲ እና ፔምበርተን ፈጠራ ንፅፅር
ካልዲ እና ፔምበርተን ምንም እንኳን በጂኦግራፊ እና በዘመናት ቢለያዩም አስደናቂ ምስስሎሽ አላቸው። ሁለቱም የማወቅ ጉጉት ያላቸው ቀማሚዎች ናቸው። ሁለቱም በመጠጥ ኢንዱስትሪው ውስጥ አብዮት አፈንድተዋል። ካልዲ በቡና፣ ፔምበርተን በኮካ ኮላ! ንግድን እና ባህልን በዓለም አቀፍ ደረጃ አስተሳስረዋል።
ሁለቱም ቀይ ምንጣፍ ይነጠፍለን፣ የክብር ዶክትሬት ይሰጠን፣ ክብር እንሸለም፣ ላብራቶሪ ይገንባልን፣ ቢሮ ይመረቅልን፣ በጀት በጅቱልን፣ ፕሮፌሰር ብላችሁ አንቆለጳጵሱን ሳይሉ ያላቸውን አስተዋይነትና ፈጣሪ አእምሮ ተጠቅመው የአለምን ጥም የሚቆርጥ መጠጥ ፈልስፈው አልፈዋል።
የኮካ ኮላ ከአትላንታ የሰፈር መጠጥነት እስከ አለም አቀፍ ምርትነት
በካንደለር የበሰለ የንግድ ስራ አመራር፣ ስልታዊ ማስታወቂያ፣ ስትራቴጂክ ብራንዲንግ እና ያላሰለሰ ጥረት ኮካ ኮላ ዛሬ ወደምናውቀው ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ሊደርስ ችሏል።
እስከዛሬ ፎርጅድ አልሰራ ያለ የኮካ ሎጎ ወጥነት እስከዛሬ የማይሰለች የማይለወጥ የጥራት አርማ ነው። እ.ኤ.አ. በ1915 የተሰራው የኮካ ኮላ ጠርሙስም ቢሆን በታሪክ በጣም አስገራሚ ከሚባሉ የማሸጊያ ዲዛይኖች አንዱ ነው። የጠርሙሱ ቅርጽ ሸንቃጣ ሴትን እንዲመስል ታስቦ ስለተነደፈ ውበትን ሰጥቶታል። ሸካራማ መሆኑ በጨለማ እንኳ ሳይቀር በቀላሉ በዳሰሳ እንዲለይ እና በቀላሉ ከእጅ እምልጦ እንዳይወድቅ ስላደረገው ኮካን ተመራጭ መጠጥ እንዲሆን አስችሎታል።
ቀደምት የኮካ ኮላ ማስታዎቂያዎች የማርኬቲንግ ጂኒየስ ነበሩ። ፈር ቀዳጅ የማስታዎቂያ ስራዎች እንደሆኑ ይታመናል። የኮካን ድብልቅ ቀመር ድብቅ አድረገው ጠርሙሶችን በፍራንቻይዝ እንዲስፋፉ መደረጉም ኮካ ኮላ ያለ ከፍተኛ የካፒታል ኢንቨስትመንት ምርቱን በአለም አቀፍ ደረጃ አሳድጓል።
ኮካ ኮላ ዘመናዊ የሸማችነትን ባህል (Consumerism) ያሰረጸ፤ የአለም አቀፍ የግብይት ስልቶችን የቀረጸ ክስተት ነው። በአላትን ከሸመታ እና በቀለማት ማሸብረቅ ጋር የምናገናኝበትን እሳቤ ላይ ትልቅ ተጽእኖ አድርጓል። የገና አባት የሚባለው ሳንታ ክላውዝ ነጭና ቀይ ቀለም ሳይቀር በኮካ ብራንድ ቀለም የተለበጠ ነው።
ኮካ ኮላ የዲፕሎማሲ መሳሪያ ጭምር ሆኖ አገልግሏል። ከቀዝቃዛው ጦርነት በኋላ ወደ ምስራቃዊ አለም ገበያዎች በመግባት የመጀመሪያው የምዕራባውያን ምርት ነው።
ግን ይህ የኮካ ታሪክ ከኢትዮጵያ ጋር ምን አገናኘው?
የቡና መገኛ እና የብዝሀ ሕይወት (Biodiversity) መነሃሪያ – ኢትዮጵያ
ኢትዮጵያ ከአገርነት ባሻገር የብርቅዬ ሕያው እጽዋት ምድር ነች። በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ የእጽዋት ዝርያዎች መኖሪያ ቤታቸው ኢትዮጵያ ናት። እነዚህ ጥሩ መዓዛና ቀለም ያላቸው እጽዋት ለአጽማችን ጥላ ከመሆን ባለፈ ልብ ላለው መድኃኒት፣ ምግብ፣ መጠጥ፣ ልብስ፣ ጌጣ ጌጥ ሊያደርጋቸው ይችላል። በመጥረቢያ እየገነደስን የምንጥላቸው ዛፎች ከወርቅ በላይ ውድ ሃብት ሊፈጥሩ ይችላሉ።
ቡናን ተመልከቱ። ኢትዮጵያ ለአለም ገበያ ካቀረበችው እጽዋት መካከል አንዱ ነው። በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ግብይት የሚካሄድበት፤ ብዙ ቢሊዮን ሃብት ያተረፈ ምርት ነው። የፍየል እረኛው ካልዲ ኮካን የፈጠረው ፔምበርተን የተወለደባት ሃገረ አሜሪካ ገና ሳትፈጠር ቡናን መርምሮ፣ ቀምሞ ለአለም አስተዋውቋል። ይህ አለም አቀፍ የቡና አብዮት የኢትዮጵያ የእጽዋት ሀብቶች (botanical treasures) የዓለምን ገበያ ሊቆጣጠሩ እንደሚችሉ ያረጋግጣል።
ከቡና በተጨማሪ ከሰፊ የብዝሀ ሕይወት ሀብቷ ተጠምቀው የሚሰሩ በርካታ ሀገር በቀል መጠጦች (ለምሳሌ ጠጅ፣ ጠላ፣ ቦርዴ፣ ሻሜታ፣ ቀሪቦ ወዘተ) በየጓዳ ከመርመስመስ ዘልቀው አለም አቀፍ ገበያ ሊገቡ ይችላሉ። የሚፈልጉት ማዳበር፣ ማበልጸግ፣ ‘ኦርጋኒክ ነው’ ብሎ መሰከስ፣ ‘በፕሮባዮቲክስ የበለፀጉ ናቸው’ ብሎ ብራንድ ማድረግ ብቻ ነው። ጌሾን ወይም ሌላ ቁጥቋጦ አሰማምሮ ቡናን የሚያስንቅ ልናደርገው እንችላለን።
ሌላው ቀርቶ መሃል አዲስ አበባ ያለው የጉለሌ እፅዋት ማእከል ብቻ የሚገኙ እጽዋትን በማጥናት ተአምር ልንሰራ እንችላለን። በየገዳማቱ እና አብያተ ክርስቲያናት የሚገኙ ጥብቅ ደኖችማ የመድኃኒት ፋብሪካ በሏቸው! ልክ እንደ ፔምበርተን ፋርማሲ የሙከራ ላብራቶሪዎች ናቸው!
የኢትዮጵያ ያልተነካ እምቅ አቅም
የተትረፈረፈ የእጽዋት ሃብት ያላት ኢትዮጵያ አሁንም ልክ እንደ ኮካ ኮላ አለምን የሚያጣፍጥ መጠጥ/ምግብ/መድሃኒት የመፍጠር አቅም አላት። ቀጣዩ አለም አቀፍ የመጠጥ ፈጠራ ከኢትዮጵያ ሊወለድ ይችላል።
የኢትዮጵያን አገር በቀል እፅዋትን ሃብት ከባህላዊ የመጠጥ አዘገጃጀት ልምዶች ጋር አዳብሎ ልዩ ጣዕም ያለው ጥም ቆራጭ መጠጥ መስራት የማይቻል አይደለም። ለጨጓራ የሚመጥን፣ ለጉበት የማይከብድ፣ በፕሮባዮቲክ የበለጸገ፣ ለአንጀት ተስማሚ አዲስ ለስላሳ መጠጥ ከኢትዮጵያ ሊመረት ይችላል። ‘Powered by Ethiopia’ የሚል አርማ ያለው ኢትዮጵያዊ መጠጥ እንደኮካ አለምን ሊያዳርስ ይቻላል።
ኢትዮጵያውያን በእጃችን ያለ ብዝሀ-ህይወትን እንደገና በመፈተሽ ድንበር ተሻጋሪ አዳዲስ ነገሮችን መፍጠር አለብን። ከአንዲት ትንሽ የአትላንታ መድሀኒት መደብር የሚሰራ ፋርማሲስት ኮካኮላን ያክል ሃብት መፍጠር ከቻለ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለ ሳይንቲስት፣ ተመራማሪ እና ስራ ፈጣሪ ቀጣዩን በአለም አቀፍ ደረጃ የሚታዎቅ መጠጥ ማምረት ይችላል።
የጸና የማወቅ ፍላጎት እና መተባበር ካለ ካልዲ በቡና ላይ እንደነገሰ፣ ፔምበርተን ኮካ ኮላን እንደፈለሰፈ ሁሉ እኛም የዛሬ ትውልድ ኢትዮጵያዊያን በአስተዉሎ በማለም፣ በመመርመር፣ በመሞከር እንደገና በማሰብ አዲስ ዓለም አቀፍ የስኬት ታሪክ ማስመዝገብ እንችላለን።
እኔ ከዚህ በኋላ የአለማየሁ ዋሴን ዝጎራ አዝዬ ጉለሌ ቦታኒካል ጋርደን ነው ውሎዬ ፡)