የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ትራምፕ ስልጣን እንደተቆናጠጡ ከፈረሟቸው ፕሬዝዳንታዊ አዋጆች መካከል ጤናን የሚመለከቱ ስር ነቀል ፖሊሲዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ መነጋገሪያ ሆነዋል። አወዛጋቢ የጤና ሚኒስቴር ከመሾም እስከ አሜሪካን ከአለም ጤና ድርጅት (WHO) ማስወጣት፤ ቁልፍ የጤና ተቋማትን ኮሚኒኬሽን ከመዝጋት እስከ የተቋማትን አካታችነት፣ እኩልነት እና ፍትሃዊነትን ለማስፈን የወጣ ፕሮግራም ማገድ ሰፊ ክርክር አስነስተዋል።
ትራምፕ በመጀመሪያው የነጩ ቤተ መንግስት ጊዜያቸው ያወጡትን አዋጅ እና በባይደን አስተዳደር የተሻረባቸውን ከWHO መውጣት አስደንጋጭ ውሳኔ በድጋሜ እንደዛቱት አድርገውታል። በዓለማችን ትልቁ ኢኮኖሚ እና አንጋፋው የጤና ተቋም መካከል ያለው ግንኙነት እንደገና ሊበጠስ ተቃርቧል።
ፕሬዚዳንት ትራምፕ አሜሪካ ከዓለም ጤና ድርጅት ለመውጣት ሂደቱን የጀመሩት ድርጅቱ የዓለም ጤና ጉዳዮችን በተመለከተ ያለውን ቸልተኝነት በመንቀፍ ነው። ትራምፕ የዓለም ጤና ድርጅት የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመግታት አፋጣኝ እና ግልጽ ስራ ባለመስራቱ ለቫይረሱ መስፋፋት አስተዋጽኦ አድርጓል ብሎ ያምናል። የቻይና ፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነት አለበትም ሲሉ ከሰዋል።
የጤና ዲፕሎማሲ፣ ሳይንሳዊ ትብብር እና የገንዘብ ድጋፍ ከመቼውም ጊዜ በላይ አንድነትን በሚጠይቅበት በዚህ ዘመን ወደፍቺ መንደርደር WHOን አቅመ ቢስ ሊያደርገው ይችላል። የዓለም ጤና ድርጅት በጀት ከአሜሪካው ሲዲሲ አመታዊ በጀት አንድ አራተኛ ያህል የማይበልጥ በገንዘብ ማነስ የሚሰቃይ ድርጅት እንደሆነ ልብ ሊሉ ይገባል።
አሜሪካ የዓለም ጤና ድርጅት መስራች አባልና ዋና ገንዘብ አዋጪ ሆና ከ75 አመታት በላይ ረድታለች። ወረርሽኞችን ለመከታተል፣ ሳይንሳዊ ግኝቶችን ለመለዋወጥ፣ ምርጥ ተሞክሮዎችን ለመቅሰም፣ የጤና ዲፕሎማሲን ለማስፋፋት የትብብሩ ዋና ተዋናይ ነበረች። ስለሆነም የአሜሪካ መውጣት የዓለም ጤና ድርጅት ፋይናንስ ጉዳት አይቀሬ ነው። በተለይ የWHOን በጀት ጉድለት የሚሞላ አማራጭ ገንዘብ ከሌሎች አባል ሃገራት ካልተገኘ አዳጋች ይሆናል።
ትራምፕ እንደሚሉት አሜሪካ ከዓለም ጤና ድርጅት አባልነት ለመውጣት መወሰኗ አሜሪካን የበለጠ ጤናማ አያደርግም ባዮችም አሉ። ይልቁንም ይህ እርምጃ የደሃ ሃገራትን የጤና ችግሮች ከማባባስ ባሻገር የአሜሪካን የመሪነት ሚናን እንደሚያዳክም ነው የሚተነበየው። አንድ ቦታ የተነሳ ወረርሽኝ የአሜሪካን ንግድና ቱሪዝም ስለሚያውክ የአሜሪካን ኢኮኖሚ በተዘዋዋሪ ሊነካው ይችላል።
የጤና ዘርፍ አንድነት መሸርሸር ዓለም አቀፍ ትብብርን የሚጠይቁ ድንበር የለሽ በሽታዎችን ለመዋጋት አስቸጋሪ ያደርገዋል። አሜሪካ ከዓለም ጤና ድርጅት አባልነት ከወጣች የተለያዩ ድንበር ዘለል ተላላፊ ወረርሽኞች ላይ የምታደርገውን ዝግጁነት እና ምላሽ ላይ የሚተባበራት አይኖርም፤ መረጃ የመለዋወጥ እድልም ማጣት ያመጣል።
ከዚህ ባሻገር አሜሪካ በUSAID እና ሌሎችም ተራድኦ ድርጅቶች በኩል የምትሰጠውን እርዳታ በቃኝ እያለች ነው። የታክስ ከፋይ አሜሪካኖችን ገንዘብ ለማንም እንካችሁ አልልም፤ ራሳችሁን ቻሉ ብላለች።
ማስተዋል ያለብን ጤና የሁሉም ሃገር የጋራ ሃላፊነት ነው። ድንበር ዘግተን የምንከላከለው ሳይሆን በጋራ ትብብር ላይ የተመሰረተ ነው። ስለሆነም ከመከፋፈል ይልቅ ትብብርን ማጠንከር ይበጃል።
በታዳጊ ሃገራት የጤና ቀውስ ይፈጥር ይሆን?
ይህ እርምጃ በአሜሪካ ድጋፍ የሚሰሩ በርካታ የጤና ዘርፎችን፣ ህክምናዎችና እና ዓለም አቀፍ የጤና ትብብር ስራዎች ላይ ችግር ሊፈጥር ይችላል ሲሉ የጤና ባለሙያዎች እና ተሟጋቾች ስጋታቸውን አንጸባርቀዋል። የአለም አቀፋዊ የበሽታ ልየታ፣ ክትትል እና ምላሽ አሰጣጥ ስርዓቶችን ያዳክማል በሚል ስጋት ፈጥሯል።
ታዳጊ ሃገራት ወረርሽኝ ኮሽ ባለ ቁጥር የባለሙያ፣ የቴክኒክ፣ የገንዘብ እና ሎጂስቲካዊ ድጋፍን ለመስጠት የሚጠብቁት የአሜሪካን እጅ ነው። ስለሆነም አሜሪካ እጇን ስታጥፍ አፍሪካ ምን ይውጣት ይሆን የሚሉ ስጋቶች እያየሉ መጥተዋል።
በWHO እና USAID በኩል ለብዙ ታዳጊ ሃገራት ከፍተኛውን የጤና ገንዘብ ድጋፍ የምታደርገው አሜሪካ እንደመሆኗ የዚህ ድጋፍ መቀነስ አስፈላጊ የጤና ፕሮግራሞች የገንዘብ እጥረት ያጋጥማቸዋል። ለምሳሌ የክትባት ዘመቻዎች፣ ኤችአይቪ/ኤድስ፣ ቲቢ እና ወባን መከላከል የመሳሰሉት ፕሮግራሞች በአሜሪካ ድጋፍ ላይ ጥገኛ ናቸው። የአሜሪካ ገንዘብ ድጎማ ከቀነሰ እነዚህ ወሳኝ የጤና አገልግሎቶች አደጋ ላይ ሊወድቁ ይችላሉ።
ከገንዘብ ባሻገር እንደወረርሽኝ ያሉ የጤና ቀውሶች ሲነሱ ፈጣን ምላሾችን የማስተባበር ሃላፊነት የአሜሪካ ነው። የአሜሪካ ድጋፍ ሲቀንስ ወረሽኝን የምንመክትበት ጉልበትና ቅልጥፍና ላይኖር ይችላል። ይህም በድሃ አገሮች እጅግ የከበረውን የሆነውን የሰው ህይወት አደጋ ላይ ይጥላል።
የጤናው ዘርፍ የውጭ እርዳታ ጥገኛ ሰለባ መሆን
ለበርካታ ዓመታት የአፍሪካ ጤና በውጭ እርዳታ ላይ የተመሠረተ ነው። የውጭ እርዳታ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት እንደታደገ አሌ የማይባል ሃቅ ነው። ግን ደግሞ የጥገኛ ጥገኛ አዙሪት ውስጥ ከቶናል። ለጤና በጀት መመደብ ሃላፊነታችን እንዳልሆነ እስኪሰማን አዘናግቶናል። የዜጎቻችንን ጤና ረስተን አሜሪካ የምታደርጊንን አርጊን ብለን ተኝተናል። መንግስታት በራሳቸው የጤና መሠረተ ልማት ላይ ኢንቨስት ከማድረግ ይልቅ በለጋሽ ሃገራት ገንዘብ የሚደገፉ ፕሮግራሞች ላይ ብቻ ቅድሚያ ሰጥተው ያቅዳሉ። አሁንም ብዙ አፍሪካዊ አገሮች መሰረታዊ የጤና ፕሮግራሞችን ለመስጠት የውጭ እርዳታ ይመጸወታሉ።
የውጭ ድጋፍ ወሳኝ ቢሆንም በእርዳታ ላይ ከመጠን በላይ መተማመን ሃገራዊ እውቀትን ሊገታ ይችላል። የውጭ እርዳታ ጥገኛነት የብሔራዊ የጤና ሥርዓቶችን እንዳይጎለብቱ ያዳክማል። ሃገር በቀል እውቀት እና አሳቤ እንዳይፋፋ በር ይዘጋል። ስለሆነም የእርዳታ ድንገት መቋረጥ ጊዜያዊ የጤና ችግሮች ሊፈጥር ቢችልም አፍሪካ የራሷን የጤና አጀንዳ እንደገና በራሷ ለመቅረጽና ከጥገኝነት ለመላቀቅ እድል ይፈጥራል።
ሰፊ ጸጋ ያላት አፍሪካ እስከመቼ በለጋሾች እርዳታ መመጽወት ትቀጥል?
የእርዳታ መቋረጥ ምን በጎ ተጽእኖ ይኖረዋል?
የውጭ ዕርዳታ በአፍሪካ ጤና ዘርፍ ብዙ ረድቷል። በአንጻሩ መንግስታት በእርዳታ ላይ አብዝተው በመተማመን ለጤና በጀት በጅተው የጤና መሰረተ ልማት ላይ እንዳይሰሩ አስንፏል። ይህ የUSAID እርዳታ መቋረት ምናልባትም በራሳችን በጀት ስራ መስራት እንድንጀምር፣ ዘላቂ የጤና መፍትሔዎችን እንደገና እንድንመረምር ሊያነቃን ይችላል።
በማደግ ላይ ያሉት ሃገራት የአጭር ጊዜ ተግዳሮቶችን የሚፈጥር ቢሆንም የጤና ስትራቴጂዎቻቸውን እና ፖሊሲያቸውን እንዲገመግሙ እድል ይሰጣል። እርዳታ ሲቋረጥ የውጭ ጥገኝነት እየቀነሱ የሀገር ውስጥ ሀብቶችን ለጤና ለመመደብ ያስገድዳል። መንግስታት ለግጭትና ጦርነት የሚውል ወታደራዊ ወጪዎች ወደ አንገብጋቢ የጤና ዘርፎች በማዞር የተሻለ ኢንቨስትመንት ፈሰስ እንዲሆን ሊያስገድድ ይችላል።
የውጭ እርዳታ ጥገኝነት መቀነስ ወደራስ ለመመልከት እድል ይሰጣል፤ በሂደት ራስን መቻል እና በራስ አቅም መተማመን ይፈጥራል። የውጭ እርዳታ ከመጠበቅ ይልቅ የሃገር ሀብቶችን በማሰባሰብ አዳዲስ መፍትሄዎችን የሚፈጥሩ የጤና ፕሮጀክቶችን መስራት ይጀምራሉ። ይህ ሃገራዊ ልምምድ ወደትልቅ ውጤት ሊያደርስ ይችላል። እንዲህ ተገደው የሰሩ አንዳንድ ሃገራት በጤና ዘርፍ ከፍተኛ እመርታ አሳይተዋል።
የአሁኑ የአሜሪካ እርዳታ መቋረጥ አፍሪካ የራሷን ጠንካራ የጤና ስርዓቶችን የምትገነባበት አጋጣሚ የሽግግር ጊዜ ቢሆን ጥሩ ነው። አዳዲስ አፍሪካዊ አጋርነት በመመስረት በጋራ ለመስራት እድል ይሰጣል። ቀጠናዊ ትብብር በመፍጠር አዲስ አፍሪካዊ እይታን ለመፈልሰፍ ሊጠቅም ይችላል። አፍሪካ የራሷን የጤና ስርአት በመምራት ዘላቂ የሆኑ አፍሪካዊ መፍትሄዎችን መገንባት ያለባት አሁን ነው። አፍሪካ ወደ ጤና ነፃነት የምትንደረደርበት ጊዜ እናድረገው።
ሌላው ማስተዋል ያለብን የዕርዳታ ኤጄንሲዎች ወጪዎች በተለምዶ አስተዳደራዊ ወጪዎች ይበዛባቸዋል። በቀጥታ ተጠቃሚው ማህበረሰብ ከሚደርሰው በጀት ይልቅ ለደሞዝ፣ ለኪራይ፣ ለስራ ማስኬጃ፣ ለስብሰባ እየተባለ የሚባክነው ገንዘብ ቀላል አይደለም። አንዳንዴ ከሲሶ በላይ የሚሆን ከልክ ያለፈ የአስተዳደራዊ ወጪ ቀጥተኛ ዕርዳታ ለታለመለት ግብ እንዳይውል ያደርጋል። ተጠቃሚው ጋር ሳይደርስ የሚባክን ገንዘብ ብዙ ነው። ለዚህ የተጋነነ አስተዳደራዊ ወጪ አንዱ ምክንያት የአፍሪካ ሃገራት የተንዛዛ ቢሮክራሲ እና የሎጂስቲክ አለመቀላጠፍ እንደሆነ ልብ ሊሉ ይገባል።
የጤና ዘርፍ ነጻነታችንን እውን ለማድረግ ምን እናድርግ?
የአሜሪካ እርዳታ መቋረጥ የአጭር-ጊዜ መረባበሽ ቢፈጥረም የረጅም ጊዜ ለውጥ ለመጀመር እና ሰከን ብሎ አፍሪካዊ መፍትሄዎችን ለማጤን ጥቅሞች አሉት። ይህ ትንሽ ፈተና ለአፍሪካ ትልቅ እድል ይሰጣል። አፍሪካ የጤና ነፃነት የምትጎናጸፍበት አዲስ ዘመን ሊያመጣ የሚችል ጥሩ አጋጣሚ ነው። አፍሪካ የእራሷን ዕጣ ፈንታ በራሷ ለመወሰን ኃላፊነት የምትወስድበት ዘመን መሆን ግድ ይላል።
አፍሪካን ከእርዳታ ጥገኛነት ነፃ ለማውጣት ተጠያቂነት ያሰፈነ አሰራርና አመራር ያስፈልጋል። የፖለቲካ ቁርጠኝነት ይፈልጋል። ፖለቲከኞች ለስልጣናቸው እንደሚሳሱት ሁሉ ለህዝባቸው ጤናም ማሰብ መጀመር አለባቸው። የአፍሪካ ባለስልጣን ቶንሲል ሲይዘው ከመቅጽበት ተሳፍሮ ወደ አውሮፓ፣ አሜሪካ ወይም ኤዥያ መብረር በመላው አፍሪካ በጣም የተለመደ ትዕይንት ነው። ለሃገራቸው ሌት ተቀን የሚተጉ ዜጎች በህክምና እጦት እየተንገላቱ መሪዎቻቸው ለህክምና በህዝብ ወጪ ወደውጭ ይተማሉ። መሪዎች ራሳቸው ለመጠቀም ፈቃደኛ ካልሆኑ ጤናው እንዴት ሊሻሻል ይችላል? ውጭ የሚታከም ባለስልጣን ለሚመራው ህዝብ ጤና ቅንጣት ሊጨነቅ አይችልም። አስገዳጅ ልዪ ሁኔታዎች ካልተከሰቱ በስተቀር ሃገር ውስጥ ታከም፣ አፍሪካ ውስጥ ታከም ማለት ይገባል። የዛኔ ጨክነን ለለውጥ መስራት እንጀምራለን። ለህዝብ ባያስብ እንኳ ለራሴ፣ ለቤተሰቤ ብሎ ይህ ይሰራ፣ ያ ይስተካከል ማለት ይጀመራል።
ጤናን የራሳችን ብሔራዊ አጀንዳ በማድረግ እንክብካቤን ለማሻሻል ለህዝባችን ጤና ሙሉ ሃላፊነት መውሰድ አለብን። ሀብቶች ውጤታማ በሆነ መንገድ ጥቅም ላይ መዋል እንዲችሉ ግልፅ ፖሊሲዎች እና ጥብቅ የቁጥጥር ስልቶች ያስፈልጋሉ።
ራስን ለመቻል የጤና መሠረተ ልማቶችን መገንባት ይጠይቃል። የግሉን ዘርፍ በማስተባበር በውጭው አለም የሚያስቀኑንን የጤና ተቋማት መመስረት ይቻላል። እንዲህ አይነት ዘላቂ ለውጦችን ለመደገፍ፣ ብቁ ባለሙያ ለማሰልጠን አሜሪካኖችም ሆነ ሌሎች አጋር አገሮች ቀና ናቸው። ለጋሾችም የመረራቸው ዝንታለም የማይለወጥ አላቂ ወጪ እኮ ነው።
የጤና ባለሙያዎችን ስልጠና ፕሮግራሞችን ማሳደግና ማብቃት ለነገ የሚባል አይደለም። የራሳችንን የጤና ባለሙያዎች ማበረታታትም ይገባል። የደለበ የባለሙያ ክህሎት እያለን በአመት አንዴ በሚመጣ የዘመቻ ህክምና ላይ ማተኮር ተገቢ አይደለም። ቢከፋም ቢለማም ለድንገቴ ህመም የሚደርሱልን የኛው ባለሙያዎች ናቸው። የጎደለህን ተምረህ ና፣ የሚቀርህን ክህሎት አጥና እያልን ማበርታት እንጂ የኛ ሃኪሞችማ?! እያልን ማንጓጠጥ የትም አያደርሰንም።
በአፍሪካ ህብረት አማካኝነት የእርስ በእርስ ትብብርን ማጎልበት በውጫዊ በጀት ላይ ከመተማመን ይሻላል። ጥርሳቸውን ነክሰው ስትራቴጂካዊ የጤና ፖሊሲና ኢንቨስትመንት ለውጦችን ያደረጉ፣ የአገር ውስጥ ፈጠራንና ሃብትን ጥቅም ላይ ያዋሉ አንዳንድ የአፍሪካ ሃገራት በከፍተኛ ሁኔታ መሻሻል እንዳላቸው አሳይተዋል። እነዚህን ቀድመው የነቁ ሃገሮች እስኪ አሳዩኝ? እንዴት ቻላችሁበት? ሩዋንዳ እንደምን ጤናዋን አበለጸገች? እያልን ከሌሎች አፍሪካዊ እህት ወንድሞቻችን መማር፣ ልምድ መቅሰም እንችላለን።
አሁን በአሜሪካ እርዳታ መቀነስ ምክንያት የተቋረጡ ፕሮግራሞችን እና ሲስተሞችን መንግስት በባለቤትነት ተረክቦ ስራ ላይ ባለው ሲስተም ውስጥ ለማስቀጠል ቢሞከር ወደፊት እንደአዲስ ለማስጀመር የሚያስወጣውን የመቋቋሚያ ወጪ ይቀንሳል፤ የሚበተኑ ሰራተኞችንም ከመፈናቀል ይታደጋል።
መንግስታት ለጦር መሳሪያ የሚበጅቱትን ገንዘብ ለአንገብጋቢ እና አጣዳፊ ወረርሽኝ መጠባበቂያ ከወዲሁ መመደብ እንደሚገባቸው መጠቆም ያስፈልጋል።
ማጠቃለያ
የአሜሪካ እርዳታ መቀነስ ባለ ሁለት ሰይፍ ነው። ለታዳጊ ሀገራት የጤና ችግሮችን የሚፈጥር ቢሆንም፣ በራስ አቅም መገንባት ላይ በማተኮር የጤና ስርዓቶቻቸውን እንደገና እንዲገመግሙ እና እንዲገነቡም እድል ይሰጣል። ሀገራት ከጥገኝነት መንፈስ ተላቀው የራሳቸውን የውስጥ አቅም እና ሀገር በቀል የመፍትሄ አማራጮች እንዲያጤኑ ተገደውም ቢሆን የሚጀምሩበት እድልን የሚከፍት ይሆናል።
ጥገኝነት ዘላቂ መፍትሄ አይሆንም። እውነተኛ ለውጥ የሚመጣው የአፍሪካ አገራት የራሳቸውን የጤና ሥርዓቶች ለማሻሻል ሙሉ ሃላፊነት ወስደው ሲሰሩ ብቻ ነው።
እያንዳንዳችን በጤናው ዘርፍ የየራሳችንን አስተዋጽኦ በማድረግ፤ አዳዲስ ሀገር በቀል ጅማሮዎችን በመደገፍ፣ መሪዎችን ለእውነተኛ ለውጥ በመታገል፣ ኢንቨስት በማድረግ አፍሪካ በውጭ እርዳታ ላይ ከመጣበቅ እንታደጋት። አፍሪካ የለጋሾችን ሃንዳውት መጠበቅ አያስፈልጋትም እንበል።
አፍሪካዊያንን የሚመጥን የጤና ስርዓት በራሳችን ለመገንባት ጊዜው አሁን ነው።
እነዚህ የትራምፕ ፖሊሲዎች በኢትዮጵያ ጤና አገልግሎት አሰጣጥ ላይ ምን አንድምታ ይኖራቸዋል ብለው ያስባሉ? ሃሳብዎትን ያጋሩን!
ተጨማሪ ምክር፣ እርምት ወይም ግብረ መልስ ለመስጠት በኢሜል፦ contact@melakutaye.com እና ስልክ፦ +251921720381 ማግኘት ይችላሉ።
የሩቅ ሰው እና መላኩ (ከአትላንታ)