የአፍሪካ መሪዎች በዚህ ሳምንት ለ38ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በአዲስ አበባ ሲሰባሰቡ በአዲስ አበቤ ኑሮ ላይ ከሚፈጥሩት የትራንስፖርት ጫና ባለፈ ወደ አእምሮ የሚመላለሰው ጥያቄ ‘ይህም ስብሰባ እንደባለፉት ዝምብሎ የተስፋ ወሬ ብቻ ይሆናል ወይስ መሪዎቻችን ተግባራዊ እርምጃ ይወስዳሉ?’ የሚለው ነው። “An Integrated, Prosperous, and Peaceful Africa” የሚለው የአፍሪካ ህብረት የተቀደሰ ርእይ በአመታዊ ንግግር ብቻ እንደማይሳካ ልብ ይሏል። የምንፈልጋትን አፍሪካ እውን ለማድረግ ብቸኛ መንገድ መስራት፣ መፈጸም፣ መተግበር ነው – Just Get Stuff Done.
እ.ኤ.አ. ኦክቶበር 2024 ኔቸር ላይ በታተመ ጽሁፍ ላይ ፒተር ሳንገር (Peter Singer) የተባለ ሳይንቲስት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) እና ሌሎችም ድርጅቶች በየአመታዊ ስብሰባቸው ላይ የሚደሰኩሩትን እቅድ ዉጤታማ በሆነ መንገድ እየሰሩ እንዳልሆነ ገልጿል። ለ2030 ከታቀዱት 17 የዘላቂ ልማት ግቦች (SDGs) ውስጥ በጣም ትንሹ ብቻ ሊሳኩ እንደሚችሉ ጠቁሞ አዲሱ የተመድ እቅድ ያቀድኩትን እንዴት ልፈጽም ብሎ ማቀድ መሆን አለበት ሲል ተችቷል። ከየሃገሩ ዜጎች በተዋጣ ገንዘብ የሚንቀሳቀሱት አለማቀፍ ድርጅቶች አንዳች አዲስ ተልዕኮ ያስፈልጋቸዋል፤ ይህም በየስብሰባ የሚያወሩትን በተግባር ማዋል፤ የጀመሩትን መጨረስ! መሆን አለበት ይመክራል።
የእኛው የአፍሪካ ህብረትም ህልም እና እቅድ ከመዘርዘር፣ ምኞትን በየአመታዊ ስብሰባ ከመደስኮር ባለፈ የተግባር እርምጃዎች ላይ ማተኮር መጀመር አለበት። ከውይይት ወደ ውጤት መሸጋገር አለብን። ያለፈውን የታሪክ ኢፍትሃዊነት ከመካካስ ባሻገር እራሳችን የፈጠርናቸውን አሁናዊ ችግሮች አፍረጥርጠን በመጋፈጥ የአፍሪካን የተትረፈረፈ ሃብት ወደ ዘላቂ ልማት እና ሁለንተናዊ ብልጽግና መቀየር ይገባል። በታሪክ ከተደረገብን ዉጫዊ ብዝበዛ ባሻገር እራሳችን ቤታችንን እየበዘበዝን ያለንበት ጊዜ አብቅቶ ለአፍሪካ እድገት የምንታትርበት አዲስ የተግባር ዘመን እውን መሆን አለበት።
እስካሁን የተሰበሰብነው ይበቃል – የተግባር ጊዜ ይሁን
ለበርካታ አመታት ስብሰባዎች በታላላቅ መግለጫዎች ያሸበርቃሉ ነገር ግን ለአፍሪካውያን ጠብ የሚል ለውጥ በተፈለገው ልክ አልመጣም። ድህነት፣ ወረርሽኝ እና ስደት አሁንም በአህጉሪቱ እንደተንሰራፋ ነው። ግጭቶች እዚህም እዚያም ይፈለፈላሉ። ትምህርት ቤት ዘግተን አማጺ እናሰለጥናለን። አሁን ግን ይብቃን! መሪዎች ከታይታ ውይይት ወደ ቆራጥ እርምጃ በመሸጋገር የአፍሪካን መጻኢ እድል መወሰን ይኖርባቸዋል።
የአለምን ሲሶ ውድ ማእድናት የታደለች አፍሪካ እንዴት በድህነት ሚሊዮኖች መሰረታዊ ፍላጎቶችን ለመግዛት ይቸገራሉ?! ማእድን በዲናር እየሸጥን እንዴት ፕላስቲክ በዶላር እንገዛለን?! ይህ መለወጥ አለበት።
በቀላሉ ልናጠፋቸው የምንችላቸው በሽታዎች የአፍሪካ መገለጫ መሆን አልነበረባቸውም። ወገባችንን ሸብ አድርገን ጤና ላይ ኢንቨስት ማድረግ ይገባል። ያማረ የጤና ፖሊሲና የተሽቆጠቆጠ ኮንፈረንስ ባሻገር እውነተኛ ስራ መስራት ለነገ የሚባል አይደለም። ውድ የአፍሪካዊያን ህይወት ሊታከም በሚችል በሽታ መቀጠፍ መቆም አለበት።
መሪዎቻችን ‘አንድም አፍሪካዊ በወባ፣ በቲቢ ወይም በረሃብ እንዳይሞት እናድርግ’ ብለው በሽታዎችን ለማጥፋት ይዝመቱ።
የአፍሪካ መሪዎች የተግባር ውሳኔዎችን ደፈር ብለው እንዲወስኑ፣ በፍጥነት ወደስራ እንዲገቡ ጫና እናድርግ።
አፍሪካ የችግሮች መፈልፈያ አህጉር ሳትሆን የፈውስ፣ የፈጠራ፣ የሰላም አህጉር እናድርጋት።
አፍሪካን ከአለም አቀፍ የሃብት፣ የፈጠራ፣ የጤና ደረጃ ማንጆነት ትሰረዝ።
መሪዎቻችን ምርጫ አላቸው ። እንደሰንበቴ አመታዊ ስብሰባ፣ ፎቶ፣ ራት እና ተስፈኛ ወሬ ብቻ! መቀጠል ወይም በተግባር የአፍሪካን እጣ ፈንታ የሚቀይር ስራ መስራት!
አፍሪካውያን ወሳኝ ለውጥ ፈጣሪ ማየት ይፈልጋሉ። ከአሁን በኋላ በአለም አቀፍ መድረክ ላይ በመሪዎቻችን እንዝህላልነት አናፍርም እያሉ ነው።
ከመሪዎቹ ባሻገር ሁላችንም የምንጫወተው ሚና አለ
የፖለቲካ አመራርን መውቀስ ቀላል ቢሆንም እውነቱ ግን የአፍሪካ ተግዳሮቶች የአመራር ማጣት ብቻ ሳይሆኑ የሁሉም ህብረተሰብ ክፍል የጋራ ችግር ናቸው።
ስንፍና እኮ ባህላችን ነው። የስራ ክህሎት ይጎለናል። ደካማ የስራ ሥነ-ምግባር ነው ያለን። ጠንክሮ መሥራት ዋጋ እንደሌለው እንሰብካለን። ይህ አስተሳሰብ ሳይውል ሳያድር መቀየር አለበት።
ለሥራ ያለን ስንኩል አመለካከቶች ለድህነታችን አስተዋጽኦ ያደርጋል። ቢሮ በሰአት ገብቶ አገሩን የሚያገለግል ማነው? የስራ ሰአት የሚያከብር ማነው? ስራ ቦታ በትጋት ተፍ ተፍ የሚል ማነው? ደንበኛውን የማያጉላላ ማን አለ? ኧረ የኛ ቀርቶ ሌላውን ስራውን አድምቶ በባለቤትነት ሃላፊነት የሚሰራውን ባላደናቀፍነው?! አልሰርቅም ከሃገሬ ያለውን ፋራ ብለን ባላሸማቅቅነው?! በአቋራጭ መክበርን እንደአራዳነት ባላየነው?!
አፍሪካን እያደኸየ ያለው ደካማ የስራ ባህላችን ነው። ድህነትን ለመቅረፍ አፍሪካ ሌላ የፖለቲካ አብዮት አትፈልግም። ይልቁንስ የስራ ባህል አብዮት ቢመጣ ድህነትን አሽቀንጥረን ልንጥለው እንችላለን። የማህበረሰብ የስራ ባህል፣ አመለካከት እና ስነ-ምግባር ለውጥ ማምጣት ነው የሚሻለን። የላቀ ምርታማነት፣ ጠንካራ የስራ ስነምግባር፣ ታታሪነት እና ቁርጠኛ ኃላፊነት ለማምጣት የጋራ ንቅናቄን ማፍጠር ነው የሚያዋጣን። የፖለቲካ አብዮት በቃን ብለን የስራ ባህል አብዮት፣ የታታሪነት አብዮት፣ የምርታማነት አብዮት ነው የሚበጀን። የትኛውም የመንግስት ለውጥ በሁሉም የህብረተሰብ እርከኖች የሚፈጠር ጠንካራ የስራ ስነምግባር፣ ምርታማነት እና ታታሪነትን ሊተካ አይችልም።
አፍሪካ ከፍ እንድትል ከተፈለገ ሁሉም ዜጋ ሀላፊነቱን በሚገባ መወጣት አለበት። የአፍሪካ ሊቃውንትም ከፍተኛ ደመወዝ ይቆረጥኝ፣ ቢሮ ይስፋልኝ፣ አልጋ ይነጠፍልኝ ከመጠየቅ ይልቅ በአርአያነት መምራት፣ በቅንነት መስራት እና ለየሀገራቸው ልማት ዋጋ መክፈል አለብን። የአፍሪካ ምሁራን መንግስትን ከመተቸት ባለፈ መመራመርና መፍጠር፣ ከመጠየቅ ባልፈ ላስተማራቸው ማህበረሰብ መፍትሄ ማቅረብ አለብን። የአፍሪካ ባለሙያ የችግሩ ተመልካቾች ከመሆን ይልቅ የመፍትሄው አካል የሚሆንበት ጊዜ አሁን ነው። ኬኔዲ እንዳለው “ሀገሬ ምን አደረገችልኝ ሳይሆን ለሀገሬ ምን አደረኩላት” እንበል።
የበቃ እና የነቃ መሪና ዜጋ ለአፍሪካ
ዘመኑን የዋጀ እውቀት፣ ክህሎትና እሳቤ ለአፍሪካ ያስፈልጋታል። ፒተር ሳንገር እንዳለው ከተለምዷዊ አሰራር ወጥቶ የገሃዱ አለም ውስብስብ ችግሮች የሚፈታ አሰራርና አመራር መከተል ይገባል።
ለተግባር ዘመን ዝግጁ እንሁን። አመታዊ ወሬ አቁሞ የዘወትር ስራ ለመስራት ጊዜው አሁን ነው! አለም ባለ በሌለ አቅሙ ወደፊት እየገሰገሰ እፍሪካ ማለቂያ የሌለው የስብሰባ መኣት ለውጥ ለማምጣት በቂ አለመሆኑን ለማሳመን አስረጅ አያስፈልገውም።
በሃገሩ የሚኮራ፣ ስራውን አክብሮ የሚሰራ፣ አምላኩን የሚፈራ መሪና ዜጋ ያድለን! አሜን!