ሃኪም መሆን የአንድ ሚሊዮን ዶላር ዋጋ ያስከፍላል

በአለም አቀፍ ደረጃ ዶክተር መሆን እንደ ትልቅ ሙያዊ ስኬት ይታያል። ህክምና ክብርና ብር የተትረፈረፈበት ዘርፍ እንደሆነ ይታሰባል። በተለይ ወረርሽኝ ሲነሳና የጤና ቀውስ ሲያጋጥም ሃኪሞች እንደ ጀግና ይንቆለጳጰሳሉ። የሃኪሞች ደሞዝም ከፍተኛ ተከፋይ ከሚባሉ ባለሙያዎች ተርታ የሚመደብ ነው። በእነዚህ ምክንያቶች ሃኪሞች የስራ ማቆም አድማ ሲመቱ ‘ወይ ጥጋብ’ ሊያስብል ይችላል። በዚህ ጽሁፍ ‘ዶክተር ከሆንክ ሃብታም መሆን ትችላልህ’ ስለሚባለው የተሳሳተ እሳቤ በማስረጃ ለማብራራት እሞክራለሁ። የዚህ ጽሁፍ አሃዛዊ ማስረጃዎች ከግርጌ ላይ የተጠቀሱ የአሜሪካ ሃገር መረጃዎች ናቸው።

 

 

ሃብታምነቱ ቀርቶ እንዲያውም አንድ ግለሰብ የህክምና ሙያን በመምረጡ ምክንያት በህይወት ዘመኑ የአንድ ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ኪሳራ ያጋጥመዋል። ዶክተር ለመሆን መወሰን አንድ ወጣት በህይወት ዘመኑ ሊፈጽማቸው ከሚችሉ የተሳሳቱ ገንዘብ ነክ (ኢኮኖሚያዊ) ውሳኔዎች  ውስጥ አንዱ ሊሆን ይችላል። ከውጭ ሲታይ የሚያምረው የህክምና ሙያ ከውስጥ ግን የማይታይ ኢኮኖሚያዊ ጫና አለው። ከፍተኛ የህክምና ትምህርት የወጪ መጋራት ክፍያ እዳ እና በረጅም ትምህርት የባከነ እድሜ ተደምሮ ህክምና ሃኪሙን የድሃ ድሃ ያደርጋል።

 

 

የህክምና ትምህርት ክፍያ እዳ

ሐኪም መሆን ከሚጠይቀው ረጅምና ፈታኝ ትምህርት ባሻገር የትምህርት ክፍያውም እንደዚያው ወገብ የሚይዝ ሸክም ነው። በአሜሪካ ያሉ የህክምና ትምህርት ቤቶች በአማካኝ ወደግማሽ ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ የትምህርት ቤት ክፍያ ይጠይቃሉ። ከወለድ ጋር ተደምሮ ሃኪሙ ይህንን እዳ ለመክፈል ለበርካታ አስርት አመታት ላብ ጠብ ያደረገበትን ደሞዙን ሲገብር ይኖራል።

 

 

በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ ለማስረዳት የአንድ ሰብስፔሻሊስት ሃኪም የህክምና ትምህርት እዳ እንደማሳያ ላቅርብ። የመጀመሪያ ዶክትሬት ለሰራበት ወደ አምሳ ሺህ ብር አካባቢ፣ ለስፔሻሊቲ ግማሽ ሚሊዮን ብር፣ ለሰብ ስፔሻሊቲ ሌላ ግማሽ ሚሊዮን ብር እዳ አለበት። ይታያችሁ ይህ እዳ የተጫነብን የሙሉ ቀን ስራ ሌት ተቀን እያገለገልን ለተማርነው ነው። ሙሉ ደሞዝ እንኳ ብንከፍል ከአስር አመት በላይ ይወስዳል ከፍሎ ለመጨረስ።

 

 

የህክምና ትምህርት ወጪ ይህ ብቻ አይደለም። የመማሪያ መጽሀፍቶች ዋጋ ውድ ነው። ከተመረቁም በኋላ የሙያ ፈቃድ ለማግኘት ወይም ለማሳደስ የሚጠየቁ ክፍያዎች የሚናቁ አይደሉም። የህክምና ሙያ የሚጠይቀውን ተከታታይ ሙያዊ ስልጠናዎች ለመውሰድ ሌላ ወጪ አለው። ሳይንሳዊ ጽሁፎችን ለማሳተም ወይም አዳዲስ የህክምና ግኝቶችን ለማንበብ አብዛኛዎቹ የህክምና ጆርናሎች ክፍያ ይጠይቃሉ።

 

 

ይህ ሁሉ ወጪ ተደማምሮ ከፍተኛ ተከፋይ ብትሆንም ኑሮን ከእጅ ወደ አፍ ያደርግብሃል። የጤና ዘርፉ ፈዋሾቹን በኢኮኖሚ ደዌ የሚቀጣ ስርዓት ነው የሚባለው ለዚህ ነው። ማህበረሰቡ የሚያየው ያልተጣራ ደሞዜን ነው ነገር ግን ገና ኪሴ ሳይገባ ተበልቷል አባቴ!

 

 

በህክምና ትምህርት የተቃጠለው ዕድል (Opportunity Cost in Medicine)

በህክምና ትምህርት እና ስልጠና ውስጥ ያለፉት ዓመታት ከሌሎች ሙያዎች ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ሃብት ማፍሪያ እድሜ ያቃጥላል። ደህና ሃኪም ለመሆን በአማካኝ ከ10 እስከ 15 አመት ስልጠና ይፈልጋል። የመጀመሪያ ዶክትሬት ለመስራት ወደ ሰባት አመት ይወስዳል፤ ስፔሻሊቲ ለመስራት ከሶስት እስከ አምስት አመት ይፈጃል፤ ሰብ ስፔሻሊቲ ለመማር ተጨማሪ ከሶስት እስከ አምስት አመት ይጠይቃል። እነዚህ የትምህርት ጊዜዎች ወሳኝ የወጣትነት እድሜን የረባ ገቢ ሳይሰራ ያልፋል፣ ጥሪት ሳይያዝ ያመልጣል፣ ኢንቨስት ሳይደረግ ተመልሶ የማይገኝ እድል ያልፋል።

 

 

ከህክምና ውጭ ያለ ሙያተኛ ገና በመጀመሪያ ሃያዎቹ እድሜ ትምህርቱን አጠናቆ ቋሚ ገቢ መስራት ይጀምራል፣ የወደፊት ካፒታል ገቢ የሚያስገኙ ቋሚ ንብረት ማፍራት ይጀምራል፣ የተለያዩ ሼሮችን/ስቶክ በመግዛት ረብጣ ገቢ የሚያስገኙ እንቨስትመንቶች ይጀምራል፣ ቤተሰብ ይመሰርታል። አንድ ሃኪም እነዚህን ተግባራት የሚጀምረው ከሰላላ አመቱ በኋላ ነው። ይህም ከሌላ ሙያተኞች ጋር ሲወዳደር ከአስር አመት በላይ ወርቃማ የኢኮኖሚ እድሎች ያመልጡታል ማለት ነው።

 

 

የእኔን ምሳሌ ባነሳ እኔ ለኢትዮጵያዬ የተሻለ ሃኪም ለመሆን እልቆ ቢስ የሆነው የህክምና ትምህርትን ለመረዳት ነጋ ጠባ ከቤተ መጽሃፍ ቤተ መጽሃፍ እየተዛለልኩ አንድስ አንድስ የሚያክሉ የህክምና መጻህፍት ገጾች ውስጥ ተወሽቄ ሳይንስ ስለቃቅም ሃይስኩል አንድ ላይ የተማርን ጓደኞቼ ጥሪት ቋጥረው፣ ቤት ሰርተው፣ ቤተሰቦቻቸውን ከድህነት ነጻ አውጥተው፣ ልጅ አሳድገው፣ ባንክ ባለሼር ሆነው … ምናለፋችሁ ‘ዶ/ር ገንዘብ ከተቸገርክ ደውልልን’ ደረጃ ላይ በሃብት ደርጅተው ጠበቁኝ። እኔ ገና ሃ ብዬ ኑሮን ልጀምር አይኔን ስገልጥ እኩዮቼ ሌላ ደረጃ ላይ ናቸው። ይህ ነው የተቃጠለው እድል (opportunity cost) የሚባለው። ይህንን ያመለጠኝን ከአስር አመት በላይ የዘገየ ሃብት የማፍራት እድል ከጡረታ እድሜዬ በፊት ለማካካስ በየወሩ ቢያንስ ከሩብ ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ማግኘት ይኖርብኛል (ይህ የሚሆነው ሌሎች ጓደኞቼ አሁን ካላቸው ንብረት ተጨማሪ ገቢ እንደማያገኙ ታሳቢ ተደርጎ ነው)።

 

 

በተጨማሪም ሐኪሞች ከስራ ውጭ ብዙ ትርፍ ጊዜ የላቸውም። ይህ ማለት ለራሳቸው የሚሆን ጊዜ ስለማይኖራቸው ስለገንዘብ እውቀታቸው አናሳ ይሆናል፣ ትርፋማ ኢንቨስትመንቶች የማድረግ ክህሎት አይኖራቸውም፣ ከሰዎች ጋር ተግባቦታቸው ዝቅተኛ ስለሚሆን ቢዝነስ መስራት ያዳግታቸዋል። ይህ ከፍተኛ ደሞዝ ተከፋይ የሆነውን ሃኪም በድህነት አዙሪት ተቀፍዶ እንዲወድቅ ያደርገዋል።

 

 

በኢኮኖሚክስ ቋንቋ ‘ጊዜ ገንዘብ ነው’ የሚባለው ለዚህ ነው። በትምህርት ያሳለፍኩትን፣ ለመአት ስልጠና የሸጥኩትን የወጣትነት እድሜዬ በደሞዝ ብዛት ማካካስ በቀላሉ የሚቻል አይደለም። ሌላው ተሯሩጦ ሃብት የሚያፈራበት እድሜ ሲገባደድ ነው ሃኪም ኑሮን እንደአዲስ የሚጀምረው። ምንም እንኳን ሐኪሞች የበለጠ ደሞዝ ቢያገኙም የማይመለሱ ወሳኝ የኢኮኖሚ እድሎች አባክነዋል። ዘግይተው የሚያገኙት ከፍተኛ ደሞዝ በገንዘብ ራስን ለመቻል አያስችልም። እድሜ ካመለጠ በኋላ የሚገኝ ረብጣ ደሞዝ ሃብታም አያደርግም። ባለግርማ ሞገሱን ነጭ ጋዎን ለማጥለቅ የተከፈለው መስዋትነት የጊዜና ገንዘብ ነጻነት አያጎናጽፍም።  ይህ ያመለጠ እድል በገንዘብ ሲሰላ ወደ ግማሽ ሚሊዮን ዶላር ይጠጋል።

 

 

ለዚህ ነው በአለም አቀፍ ደረጃ ሐኪሞች ከአመት አመት የስራ ማቆም አድማ ሲመቱ ማየት የተለመደ እየሆነ የመጣው። ክፍያ ይስተካከል ማለት የስግብግብነት ሳይሆን ጭቆና እና ድህነት በቃን በማለት ነው።

 

 

ለጤና ባለሙያዎች ኢንቨስት የማያደርግ የጤና ስርዓት አይወድቁ ውድቀት አደጋ ከመፈጠሩ በፊት አጥጋቢ መፍትሄ መስጠት ይኖርበታል። ሃኪምን በሮቦት ሙሉ በሙሉ መተካት እስከሚቻል ድረስ እያንዳንዱ ሀገር ይህንን መራራ እውነት መገንዘብ እና ላብን የሚያብስ በቂ ክፍያ መክፈል ይገደዳል። ፈዋሹን ልንፈውሰው ይገባል።

 

 

በአንድ ደሞዝ ሶስት ስራ

ሃኪምነት ፏ ያለ ጋዎን ደርቦ ዘናጭ ስቴቶስኮፕ ጣል አድርጎ ለህመሞች ስም ማውጣት፣ ምርመራ ማዘዝና መድሃኒት መጻፍ ብቻ አይደለም። ይህ የማከም ተግባር በጣም ትንሹ የህክምና ስራ ክፍል ነው። ማከም ለአብዛኛው ባለሙያ የሚያማርር አይደለም። የግብአት እጥረት እና መስተጓጎል በቀር ማከም የሚያስደስት ሙያ ነው።

 

 

እያከምክ አስተምር ይልሃል። ተቋሙ የሚክፍለክ ወይ ለምታስተምርበት (ዩኒቨርሲቲ ከሆንክ) አሊያል ለምታክምበት (መደበኛ ሆስፒታል ተቀጣሪ ከሆንክ) ብቻ ነው። ለሌላኛው ግማሽ ስራ አሎዋንስ ብሎ ከአንድ ሺህ ብር የማይበልጥ ይወርወርልሃል። ከህክምና ተቋማት ውጭ እንዲህ ሁለት ስራ በአንድ ደሞዝ የሚያሰራ የለም።

 

 

ሌላኛው አዛ ስራ የአስተዳደራዊ ሃላፊነቶች ናቸው። የህክምና ተቋማት እንደሌሎች መስሪያ ቤቶች ምክትል፣ ጸሃፊ፣ አሲስታንት ምናምን የሚባሉ የስራ ዘርፎች የሉትም – በተለይ ታችኛው የስራ ክፍላት። ስለዚህ ሁሉም አስተዳደራዊና የማስተባበር የማስተናገድ ስራዎች ራሱ ባለሙያው ላይ ይወድቃሉ። ይህ በጣም የምጠላው ስራ ነው፣ ከህክምናዉም ከማስተማሩም የሚያናጥበኝ ስነሆነ ያሰጠላኛል። የፖለቲካ ካድሬ እንደሆንኩ ይሰማኛል። ሪፖርት የሚያጠናክረው፣ ኦክስጂን የሚጎትተውም፣ ደም የሚያመላልሰውም፣ አልጋ የሚገፋዉም ያው ራሱ ዋና ባለሙያው ነው። ገንዘብ አዋጥቶ፣ ለምኖ የሚያሳክመዉም ራሱ ሃኪሙ! የህክምና ተቋማት አስተዳደራዊ ስራዎች ሙሉ በሙሉ ለሚመለከታቸው ድርጅቶች መተላለፍ (outsourcing) ጥሩ ይመስለኛል።

 

 

የሃኪምነት ሕልምን እንደገና ማሰብ

ሐኪምነት በጣም የተከበረ ሙያ ነው። እኔስ ቢቻለኝ በነጻ ማገልገል ልባዊ ፍላጎቴ ነው። ድጋሜ እድል ቢሰጠኝ የምመርጠው ሙያ ህክምና ነው። የዚህን ያህል ህክምና ውስጤ ነው። ግን አሁን ላይ በነጻ አይደለም በደሞዝ አልቻልኩም ነው አመጻው። እውነታው ህክምና ከፍተኛ መሥዋዕትነት የሚያስከፍል ሥራ ነው። በገንዘብ ያስርብሃል፤ በጊዜ ይደቁስሃል፤ ስሜትህን ጫና ያበረታብሃል። ወደ አንድ ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ የማይታይ የገንዘብ ጉዳት ያደርስብሃል።

 

 

ወደፊት ነጭ ጋዎን ለመልበስ ለምትፈልጉ ታዳጊዎች የህክምና ስራ እርካታ እንዳለው ጥርጥር ባይኖርም ከሙያዊ ፍቅር ባለፈ የጤና ባለሙያ መሆን ብቻውን ጥሩ የገንዘብ ምንጭ እንደማይሆን አምናችሁ ግቡበት። ከባለሙያነት ባሻገር ከጤና ጋር የተያያዙ ምርምሮች፣ ፈጠራዎች፣ ንግድ (የግል ጤና ተቋም ማቋቋም)፣ የህክምና ግብአቶች ማምረት ወይም ማቅረብ፣ የጤና ኢንሱራንስ ስራ መስራት፣ የአማካሪነት ስራዎች ወዘተ ግን በአለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ትርፍ የሚያስገኙ ዘርፎች ናቸው።  

 

 

የስልጣን ሁሉ ባለቤት የሆንከው የኢትዮጵያ ህዝብም ከደሞዝ ቁጥር በላይ ሃኪሙ የከፈለውን መስዋትነት ታሳቢ ያደረገ የኢኮኖሚ ጥያቄያችን ይሁንታ ያገኝ ዘንድ ድጋፍህን ለግስ። አቅም በፈቀደ መጠን የጤና ባለሙያውም ሆነ ሌላው ሰራተኛ የማያሳቅቅ ኑሮ የሚደግፍ ደሞዝ ይቋደስ ዘንድ ጎትጉት።  

 

 

በምርጫ ካርድ የሾምናቸሁ የተከበራችሁ አለቆቻችንም ወደመረጣችሁ ባለሙያ ተመልከቱ፤ የጤና አገልግሎት ካለጤና ባለሙያው ምንም ነው። እንዲያው ሌላው ቢቀር ‘እኔ ልራብልህ፣ እኔ ልጠማልህ፣ እኔ ልታረዝልህ’ ብሎ ማዳመጥ፣ ማስተዛዘን እና የጋራ መፍትሄ መፈለግ ይበጃል።

 

 

ማስታወሻ፦ በዚህ መጣጥፍ ላይ የተካተቱት ሀሳቦች ለአጠቃላይ መረጃ ብቻ ናቸው። ለግል ምርመራ ወይም ህክምና ዶ/ር መላኩ ጋር በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የስኳር ህክምና ክፍል መመካከር ይችላሉ።

 

 

በመረጃ የተደገፉና የተረጋገጡ ተግባራዊ የጤና ምክሮችን በዶ/ር መላኩ

Blog, Telegram, YouTube & Tiktok ይከታተሉ።

 

 

ዋቢ

https://www.cbsnews.com/news/1-million-mistake-becoming-a-doctor

https://www.whitecoatinvestor.com/

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top