ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በዓለማችን ተላላፊ በሽታዎች አስጊ የሆነ ወረርሽኝ እያስከተሉ መጥተዋል። የኮቪድ 19 ወረርሽኝ የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው።
በቀድሞ አጠራሩ የዝንጀሮ ፈንጣጣ ሲባል የነበረው በሳይንሳዊ ስሙ ኤምፖክስ በሽታ በአፍሪካ አንዳንድ ክፍሎች በማንሰራራት እንደገና አለም አቀፋዊ የጤና ስጋት ደቅኗል። እኤአ ከ2022 በፊት በአንዳንድ የመካከለኛው አፍሪካ አካባቢዎች ተወስኖ የነበረው ይህ ተላላፊ በሽታ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ድንበር ተሻጋሪ በሽታ ኖኗል።
በዚህም አሳሳቢነት ምክንያት የአለም ጤና ድርጅት እኤአ በጁላይ 23፣ 2022 አለም አቀፍ አስቸኳይ የጤና ስጋት (Public Health Emergency of International Concern) መሆኑን እንዳወጀ ነው። የአፍሪካ ሽታዎች ቁጥጥር እና መከላከል (ሲዲሲ) በበኩሉ የኤምፖክስ በሽታን አህጉራዊ አስቸኳይ የጤና ስጋት መሆኑን ካዎጀ ድፍን አንድ አመት ሊሞላው ተቃርቧል።
የኤምፖክስ (mpox) በሽታ ምንድን ነው?
የኤምፖክስ በሽታ በቫይረስ አማካኝነት የሚመጣ ተላላፊ በሽታ ነው። ቫይረሱ ለመጀመሪያ ጊዜ በ1950ዎቹ በዝንጀሮዎች ላይ ነበር የተገኘው።
ይህ በሽታ ዘር፣ ሃይማኖት፣ እድሜና ጾታ ሳይለይ ማንኛውንም ሰው ሊይዝ ይችላል። ደግነቱ ብዙ ሰዎች ሙሉ በሙሉ ይድናሉ፣ አንዳንዶቹ ግን በጸና ሊያምና ሊከፋባቸው ይችላል። በሽታው በተለይ ህጻናት፣ ነፍሰ ጡር እናቶችና የበሽታ መከላከል አቅማቸው የተዳከመ ሰዎች ላይ ይበረታል።
የኤምፖክስ ቫይረስ ብዙ አይነት ዝርያዎችና አይነቶች ያሉት ክሌድ 1 (Clade I ) እና ክሌድ 2 (Clade II) ተብለው ሊከፈሉ ይችላሉ። ክሌድ 1 ከክሌድ 2 ጋር ሲነጻጸር በተላላፊነቱ፣ የስርጭት መጠኑ፣ የከፋ ህመም የማስከተል እድሉ እና ገዳይነቱ ባስ ያለ ነው።
በኢትዮጵያ የተገኘው ዝርያ አይነት ክሌድ 1 ቢ (Clade Ib) የተባለው አይነት እንደሆነ ተረጋግጧል። ይህ በአገራችን የተገኘው የኤምፖክስ ዝርያ ከሌሎች የኤምፖክስ ቫይረስ አይነቶች ጋር ሲነጻጸር በአንጻሩ ተላላፊነቱ እና ገዳይነቱ ከፍ ያለ ነው። ይህ ማለት ኢትዮጵያ የትሻለ ዝግጅትና የተቀናጀ ምላሽ መስጠት እንዳለባት የሚጠቁም ነው።
ኤምፖክስ እንዴት ይተላለፋል?
የኤምፖክስ በሽታ ተላላፊ ህመም ሲሆን በሽታው ካለበት ሰው ወይም እንስሳ በንክኪ ሊይዘን ይችላል። በዋናነት የሚተላለፈው በበሽታው ከተያዘ ሰው ጋር በሚደረግ የቅርብ ንክኪ ነው።
- ከታማሚ ሰው የቆዳ ቁስል ወይም የሰውነት ፈሳሾች አማካኝነት በቅርብ ቀጥተኛ ንክኪ ማድረግ። ለአብነትም መሳሳም፣ መተቃቀፍ፣ በግብረ ሥጋ ግንኙነት እና በቆዳ ለቆዳ ንክኪ ይተላለፋል።
- የተያዘ ሰው ተጠቅሞባቸው ከተበከሉ ቁሳቁሶች፡ ልብስ፣ የቤት እቃዎችን፣ የምግብ እቃዎችን ና ሌሎች ግኡዝ ነገሮችን በመንካት እና በመጋራት ሊተላለፍ ይችላል።
- በበሽታው ከተያዘ ሰው የመተንፈሻ አካላት ብናኞች ማለትም በበሽታው የተያዘ ሰው ፊት ለፊት ከተነፈሰብን፣ ካሳለብን፣ ካስነጠሰብን ማለት ነው።
- ነፍሰ ጡር አናቶች ቫይረሱን ወደ ጽንሱ ሊያስተላልፉ ይችላሉ።
- የታመሙ የዱር እንሣት በሽታውን ወደሰው ሊያስተላልፉ ይችላሉ። ለምሳሌ ከቧጨሩን፣ ከነከሱን ወይም ስጋቸውን ከበላን ሊያስይዙን ይችላሉ።
የበሽታው ምልክቶች ምንድን ናቸው?
የበሽታው ምልክቶች መታየት የሚጀምሩት አንድ ሰው ለቫይረሱ ከተጋለጠ ከሳምንት በኋላ ሲሆን አንዳንዴ በቶሎ ወይም ሌላ ጊዜ ዘግየት ብሎ ሊጀምር ይችላሉ። የተለመዱ ምልክቶች የሚከተሉት ናቸው፤
- ትኩሳት፣ ብርድ ብርድ ማለት፣ ራስ ምታት፣ የመገጣጠሚያ ህመምና ድካም
- የጉንፋን ዓይነት ምልክቶች
- ቆዳ ላይ የሚወጣ ቁስል / ሽፍታ ዋነኛው መገለጫው ነው። ይህ የቆዳ ምልክቶች መጀመሪያ ላይ ጠፍጣፋ ቀላ ያለ ሽፍታ ሆኖ ይጀምርና ከዚያ አብጦ ፈሳሽ ይቋጥራል። በመቀጠልም ይፈርጥና ይቆስላል። ይህ ቁስል በፊት ላይ፣ በአፍ ውስጥ፣ እና እንደ እጆች፣ እግር፣ ደረት፣ የመራቢያ አካላት ወይም ፊንጢጣ ያሉ ሌሎች የአካል ክፍሎች ላይ ሊወጣ ይችላል። ቁስሉ በጣም ህመም ያለውና የሚያሳክክ ሊሆን ይችላል። ቁስሉ ሲቆይ ይደርቅና ተቀርፍቶ ይወድቃል። ከዚያም በአዲስ ቆዳ ይተካል።
- የተለያዩ ቦታዎች ላይ የሚዎጡ የእባጭ ንፍፍፊቶች ማበጥ
ምልክቶቹ ብዙውን ጊዜ ከ2-4 ሳምንታት ይቆያሉ።
ከቁስሉ ላይ ናሙና በመውሰድ በላብራቶሪ ምርመራ ማድረግ ይችላል።
ህክምናው ምንድር ነው?
ይህ ቫይረስ እንዳብዛኛዎቹ ቫይረሶች ሁሉ ፈዋሽ መድሃኒት አልተገኘለትም። ህክምናው በዋናነት የተያዘውንን ሰው ኳራንቲን በማድረግ እንዲያገግም የሚረዱ እንክብካቤዎችን በማድረግ ነው። ለታማሚው ቀላል ማስታገሻዎች ይበቁታል። የትኩሳት ማብረጃ መድሃኒት መውሰድ ወይም የህመም ማስታገሻ መዋጥ በቂ ሊሆን ይችላል። በተለይም ፈሳሽ በደንብ መውሰድ ይጠቅማል። ህመሙ ለጸናባቸው ታካሚዎች ሆስፒታል ማስገባትና ጸረ፟ቫይረስ መድሃኒት ሊታዘዝላቸው ይችላል።
የኤምፖክስ መከላከያ መንገዶች
እያንዳንዱ ግለሰብ የበሽታው መከላከያ መንገዶችን ተግባራዊ በማድረግ ራሳችንን እና የምንወዳቸውን ሰዎች ጤና መጠበቅ እንችላለን። አብዛኛዎቹ የኤምፖክስ መከላከያ መንገዶች ከኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ 19) ጋር ተመሳሳይ ስለሆኑ የኮቪድ 19 ልምዳችንን ለዚህ ኤምፖክስ ቫይረስ መከላከያ መጠቀም ይቻላል።
ዋነኛው መከላከያ መንገዳችን የኤምፖክስ በሽታ ምልክቶች ከሚያሳዩ ሰዎች ጋር የቅርብ ንክኪና ግንኙነት አለማድረግ ነው። ቁስሎች እስኪድኑ እና አዲስ ቆዳ እስኪወጣ ድረስ በበሽታው የተያዘ ሰው ኳራንቲን መደረግ አለበት፣ ይህ ከ 3-4 ሳምንታት ሊወስድ ይችላል። ወረርሽኙ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ከትዳር ዉጭ ከማናውቃቸው ግለሰቦች ጋር የግብረ ስጋ ግንኙነት አለማድረግ ይመከራል።
በሽታው የተገኘበት ሰው ሊያደጋቸው የሚገቡ ጥንቃቄዎች
- ከተቻለ በቤት በተለዬ ክፍል ውስጥ ኳራንቲን በማድረግ ከሌሎች ጋር የቅርብ ግንኙነት ከማድረግ መቆጠብ።
- እጅን በተደጋጋሚ በሳሙና እና በውሃ ይታጠቡ ወይም በሳኒታይዘር እጅ ማጽዳት።
- ማስክ ማድረግ።
- ከሌሎች ጋር የምንጋራቸው እቃዎች መኖር የለበትም።
የኤምፖክስ ክትባት መውሰድ ኢንፌክሽንን ለመከላከል ይረዳል። ክትባቱ በተለይም በሽታው ካለበት ሰው ጋር በተገናኘን በ4 ቀናት ውስጥ መሰጠት አለበት። ይህ ክትባት ከፍተኛ ተጋላጭ ለሆኑ ግለሰቦች ለምሳሌ የጤና ባለሙያዎች ይመከራል።
ማጠቃለያ
የኤምፖክስ በሽታ ስርጭቱ እየሰፋ ቢሆንም መደናገጥ አያስፈልግም። በበሽታው የተያዙ አብዛኛዎቹ ሰዎች ሙሉ በሙሉ ይድናሉ። አብዛኛውን ጊዜ ለሞት የሚዳርግ አይደለም።
በተገቢው የግንዛቤ እና የመከላከያ እርምጃዎች እራሳችንን እና ማህበረሰባችንን መጠበቅ እንችላለን። አንዴት እንደሚተላለፍ በመረዳት፣ ምልክቶቹን በማወቅ እና የመከላከያ እርምጃዎችን በመውሰድ ቫይረሱን ለመከላከል፣ ስርጭቱን ለመቆጣጠር እና የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ የሚረዱን ዘዴዎች በእጃችን ናቸው።
እርስዎ ወይም የሚያውቁት ሰው የኤምፖክስ ምልክቶች ካሳዩ ወዲያውኑ የጤና ባለሙያ ምክር ይጠይቁ። በነጻ የስልክ መስመር 8335 ወይም 952 በመደዎል ያሳውቁ፣ እርዳታ ያግኙ። የጤና ሚኒስቴር የሚያወጣቸውን መመሪያ ይከተሉ።
ማስታወሻ፦ በዚህ መጣጥፍ ላይ የተካተቱት ሀሳቦች ለአጠቃላይ መረጃ ብቻ ናቸው። ለግል ምርመራ ወይም ህክምና ዶ/ር መላኩ ጋር በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የስኳር ህክምና ክፍል መመካከር ይችላሉ።
በመረጃ የተደገፉና የተረጋገጡ ተግባራዊ የጤና ምክሮችን በዶ/ር መላኩ
Blog, Telegram, YouTube & Tiktok ይከታተሉ።
ተጨማሪ ምክር፣ እርምት ወይም ግብረ መልስ ለመስጠት በኢሜል፦ contact@melakutaye.com ማግኘት ይችላሉ።
ይህን መረጃ ጠቃሚ ሆኖ ካገኙት ለሌሎች ያጋሩ።
Dear melakutaye.com Admin!
Greetings. Good to connect with you