የኤምፖክስ (mpox) በሽታ የቆዳ ሽፍታ

የኤምፖክስ በሽታ በቫይረስ አማካኝነት የሚመጣ ተላላፊ በሽታ ነው። የበሽታው ምልክቶች መታየት የሚጀምሩት አንድ ሰው ለቫይረሱ ከተጋለጠ ከሳምንት በኋላ ሲሆን አንዳንዴ በቶሎ ወይም ሌላ ጊዜ ዘግየት ብሎ ሊጀምር ይችላሉ።


የኤምፖክስ ምልክቶችን ለመጥቀስ ያክል ትኩሳት፣ ብርድ ብርድ ማለት፣ ራስ ምታት፣ የመገጣጠሚያ ህመምና ድካም ፣ ጉንፋን መሰል ምልክቶች ይገኙበታል። ቆዳ ላይ የሚወጣ ቁስል / ሽፍታ የኤምፖክስ በሽታ ዋነኛው መገለጫው ነው። በዚህ ጽሁፍ የኤምፖክስ ዋነኛ ምልክት ስለሆነው የቆዳ ሽፍታ በዝርዝር እናያለን።


የኤምፖክስ ሽፍታ ከሌሎች ቆዳ ላይ ከሚዎጡ ሽፍታዎች ልዩ ነው። ከሌሎች የኤምፖክስ ምልክቶች ሁሉ በጣም የተለመደው እና በግልጽ የሚለይ ነው። ስለሆነም የኤምፖክስን የቆዳ ሽፍታ መገለጫዎች መረዳት ህመሙን በቶሎ ለመለየት፣ ቅድመ ጥንቃቄዎች ለማድረግ እና አፋጣኝ ህክምና ለማግኘት ይረዳል።


የኤምፖክስ ሽፍታዎች በየትኛውም የሰውነት ክፍል ላይ ሊወጡ ይችላሉ በተለይም በፊት ላይ፣ በአፍ ውስጥ፣ እጆች፣ እግር፣ ደረት፣ ጀርባ፣ የመራቢያ አካላት፣ ፊንጢጣ እንዲሁም ሌላ የሰውነት ክፍላችን ላይ ሊወጣ ይችላል። በጣም ህመም ያለውና የሚያሳክክ ሊሆን ይችላል።


የኤምፖክስ ሽፍታዎች አምስት ደረጃዎች አሉት። የአምስቱ ደረጃዎች ሂደት ከሁለት እስከ አምስት ሳምንታት ሊወስድ ይችላል። በሁሉም ደረጃዎች በሽታው ሊተላለፍ ይችላል።


ደረጃ 1፡ ጠቃጠቆ ሽፍታ (macule)

ይህ የኤምፖክስ ሽፍታ የመጀመሪያው ምልክት ሲሆን ጠፍጣፋ ቀላ ያለ ሽፍታ ነው። ቆዳው ቀለሙ ሲቀየር ይታወቃል ማለትም ቆዳው እንደመቆጣት ብሎ ይቀላል። በዙሪያው ካለው ኖርማል ቆዳ ጋር ሲነጻጸር እብጠት ነገር የለውም። እንደማንኛውም አለርጂ ወይም የቆዳ መቆጣት ሊመስል ይችላል።


ይህ ደረጃ ከ2-3 ቀናት በሁኋል ወደሚቀጥለው ደርጃ ይለወጣል።


ደረጃ 2፡ ጠጣር እባጭ (Papule)

አሁን ሽፍታው ያብጥና እንደብጉር ጉብ ይላል። ሲነኩት ጠጠር ያለ ይሆናል። በመዳፍ ሲዳሰስ ከዙሪያው ካለው ኖርማል  ቆዳ ተለይቶ ከፍ ያለ እባጭ ይሆናል።


ከጥቂት ቀናት በኋላ እህ እባጭ ፈሳሽ ቋጥሮ ወደሚቀጥለው ደረጃ ይለወጣል።


ደርጃ 3፡ ፈሳሽ የቋጠረ እባጭ (Vesicle)

ይህ ሽፍታ ውሃ የቋጠሩ እባጮች የሚታዩበት ደረጃ ነው። እነዚህ ሽፍታዎች አንዳንዴ እጃችን እሳት ወይም የፈላ ዉሃ ሲያቃጥለን የሚዎጡት አይነት ዉሃ የቋጠሩ እባጮች ናቸው።


ከጥቂት ቀናት በኋላ ወደሚቀጥለው ደረጃ ይለወጣል።


ደራጃ 4፡ መግል የቋጠረ እባጭ (Pustules)

አሁን ሽፍታው መግል ይቋጥራል። ከደረጃ ሶስት እባጮች የበለጠ እየተለቁና ህመም እያመጡ ይሄዳሉ። ቢጫማ/ነጭማ መግል እየያዙ ያድጋሉ። የእባጩ አናት ላይ እንደእምብርት ግብት የሚል ቅርጽ ያወጣሉ። መግሉ የሚፈጠረው ሰውነታችን የኤምፖክስ ቫይረሱን ለማጥፋት የሰውነታችን በሽታ መከላከል ሂደት በሚያደርገው ትግል ነው።


ይህ ሽፍታ ውሎ አድሮ ከሳምንት በኋላ ይፈርጥና ይቆስላል።


ደረጃ 5፡ መቁሰልና መድረቅ (scab, scarring and healing)

ደረጃ 4 ላይ የነበረው እባጭ ይፈርጥና ይቆስላል። ቁስሉ ሲቆይ ይደርቅና ሻካራ፣ ጠቆር ያለ ቅርፊት ይሰራል። በኋላ ተቀርፍቶ ይወድቃል። ከዚያም በአዲስ ቆዳ ይተካል። ይህ ሂደት አንድ ወይም ሁለት ሳምንት ይወስዳል።


አንዳንድ ሰዎች ላይ አነስተኛ ጠባሳ ሊተው ይችላል። በተለይ እያከክን ከነካካነው እና ካለጊዜ ከቀረፋነው ጠባሳ ይጥላል። ይህ እንዳይሆን ቆዳው በራሱ ጊዜ እንዲያገግም ጊዜ መስጠት ይፈልጋል።


የኤምፖክስ መከላከያ መንገዶች

እያንዳንዱ ግለሰብ የበሽታው መከላከያ መንገዶችን ተግባራዊ በማድረግ ራሳችንን እና የምንወዳቸውን ሰዎች ጤና መጠበቅ እንችላለን። አብዛኛዎቹ የኤምፖክስ መከላከያ መንገዶች ከኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ 19) ጋር ተመሳሳይ ስለሆኑ የኮቪድ 19 ልምዳችንን ለዚህ ኤምፖክስ ቫይረስ መከላከያ መጠቀም ይቻላል።


ዋነኛው መከላከያ መንገዳችን የኤምፖክስ በሽታ ምልክቶች ከሚያሳዩ ሰዎች ጋር የቅርብ ንክኪና ግንኙነት አለማድረግ ነው። ቁስሎች እስኪድኑ እና አዲስ ቆዳ እስኪወጣ ድረስ በበሽታው የተያዘ ሰው ኳራንቲን መደረግ አለበት፣ ይህ ከ 3-4 ሳምንታት ሊወስድ ይችላል። ወረርሽኙ በተከሰተባቸው አካባቢዎች ከትዳር ዉጭ ከማናውቃቸው ግለሰቦች ጋር የግብረ ስጋ ግንኙነት አለማድረግ ይመከራል።


በሽታው የተገኘበት ሰው ሊያደጋቸው የሚገቡ ጥንቃቄዎች

  • ከተቻለ በቤት በተለዬ ክፍል ውስጥ ኳራንቲን በማድረግ ከሌሎች ጋር የቅርብ ግንኙነት ከማድረግ መቆጠብ።
  • እጅን በተደጋጋሚ በሳሙና እና በውሃ ይታጠቡ ወይም በሳኒታይዘር እጅ ማጽዳት።
  • ማስክ ማድረግ።
  • ከሌሎች ጋር የምንጋራቸው እቃዎች መኖር የለበትም።

ማጠቃለያ

በተገቢው የግንዛቤ እና የመከላከያ እርምጃዎች እራሳችንን እና ማህበረሰባችንን መጠበቅ እንችላለን። አንዴት እንደሚተላለፍ በመረዳት፣ ምልክቶቹን በማወቅ እና የመከላከያ እርምጃዎችን በመውሰድ ቫይረሱን ለመከላከል፣ ስርጭቱን ለመቆጣጠር እና የሚያስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ የሚረዱን ዘዴዎች በእጃችን ናቸው።


እርስዎ ወይም የሚያውቁት ሰው የኤምፖክስ ምልክቶች ካሳዩ ወዲያውኑ የጤና ባለሙያ ምክር ይጠይቁ። በነጻ የስልክ መስመር 8335 ወይም 952 በመደዎል ያሳውቁ፣ እርዳታ ያግኙ። የጤና ሚኒስቴር የሚያወጣቸውን መመሪያ ይከተሉ።


ማስታወሻ፦ በዚህ መጣጥፍ ላይ የተካተቱት ሀሳቦች ለአጠቃላይ መረጃ ብቻ ናቸው። ለግል ምርመራ ወይም ህክምና ዶ/ር መላኩ ጋር በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የስኳር ህክምና ክፍል መመካከር ይችላሉ።


 በመረጃ የተደገፉና የተረጋገጡ ተግባራዊ የጤና ምክሮችን በዶ/ር መላኩ

Blog, Telegram, YouTube & Tiktok ይከታተሉ።


ተጨማሪ ምክር፣ እርምት ወይም ግብረ መልስ ለመስጠት በኢሜል፦ contact@melakutaye.com ማግኘት ይችላሉ።

ይህን መረጃ ጠቃሚ ሆኖ ካገኙት ለሌሎች ያጋሩ።

1 thought on “የኤምፖክስ (mpox) በሽታ የቆዳ ሽፍታ”

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top