ፕሮላክቲኖማ (Prolactinoma)

ፕሮላክቲን (Prolactin) ሆርሞን ምንድን ነው?

 

ፒቱታሪ እጢ (pituitary gland) አንጎላችን ውስጥ የሚገኝ ትንሽ መጠን ያለው አተር የሚያክል ሆርሞን የሚያመነጭ የአካል ክፍላችን ነው። በርካታ ጠቃሚ ሆርሞኖችን ያመነጫል። የሚያመነጫቸው ሆርሞኖች የበርካታ ሌሎች የሆርሞን የሚያመነጩ እጢዎችን ተግባር ይቆጣጠራል።


ፒቱታሪ እጢ ሆርሞኖችን አምርቶ በቀጥታ ወደ ደም ውስጥ ይለቃል። ከዚያም እንቅርትና ሌሎችም የምናውቃቸው የሆርሞን አመንጭ ክፍሎቻችን በርካታ አስፈላጊ ሆርሞኖችን እንዲያመነጩ የሚያዝዘው ፒቱታሪ ግላንድ ነው። የሰውነት ሆርሞን ስርአትን ከላይ ሆኖ የሚቆጣጠርና የሚያሳልጥ ወሳኝ አካላችን ነው። የሌሎች ሆርሞን የሚያመነጩ እጢዎች በሙሉ አለቃ (the master gland) ነው።


ይህ ፒቱታሪ እጢ ወደ ስድስት የሚደርሱ አስፈላጊ ሆርሞኖች ያመነጫል። ከነዚህ የፒቱታሪ ሆርሞኖች አንዱ ፕሮላክቲን (prolactin) ነው። ፕሮላክቲን ለጡት እድገት እና የጡት ወተት እንዲያግት የሚያነቃቃ ሆርሞን ነው። ጡት የምታጠባ እናት ወተት እንዲኖራት የሚያስችለው ሆርሞን ፕሮላክቲን ነው።

 

የኖርማል ፕሮላክቲን መጠን በወንዶችና ጡት በማያጠቡ/ነፍሰ ጡር ባልሆኑ ሴቶች በጣም ዝቅተኛ (<20 ng/mL) ነው። እርጉዝ በሆኑ ወይም ጡት በሚያጠቡ ሴቶች የፕሮላክቲን መጠን ከፍ ይላል።


ፕሮላክቲኖማ (prolactinoma) ምንድን ነው?

 

ፕሮላክቲኖማ የሚባለው የፒቱታሪ እጢ ጤናማ ያልሆነ እድገትና እብጠት (ካንሰር ያልሆነ) ሲያመጣ የሚከሰት የህመም አይነት ሲሆን የፕሮላክቲን ሆርሞን ከመጠን በላይ ይለቃል። በሌላ አጠራር ‘Prolactin-producing adenomas’ ወይም “lactotroph adenoma” ይባላል።

 

ይህ ከመጠን በላይ የሆነ ፕሮላክቲን ክምችት በሰውነት ውስጥ ያሉ በርካታ ተግባራትን ሊያስተጓጉል ይችላል። በሰውነት ውስጥ በጣም ብዙ ፕሮላክቲን ሲኖር የወንድ ወይም ሴት ሆርሞኖች መጠንና ተግባር ላይ ጣልቃ ሊገባ ይችላል። በወንዶች የቴስቶስቴሮን መጠን በሴቶች የኢስትሮጅን መጠን ይቀንሳል።

 

ሴቶች የወር አበባ ዑደት መዛባት፣ የወር አበባቸው ሙሉ በሙሉ ሊቆም ወይም መሃንነት ሊያስከትል ይችላል። አንዳንድ ሴቶች እርጉዝ ሳይሆኑ ወይም ጡት የማያጠቡ ሆኖ ሳለ የጡት ወተት መፍሰስ (galactorrhea) ያመጣል። ገና እድሜያቸው ሳይደርስ የማረጥ ምልክቶች ሊያመጣ ይችላል። በጣም ባስ ሲል የአጥንት መሳሳት ያስከትላል።

 

ወንዶች ላይ ፕሮላክቲኖማ  የዘር ፍሬ ተግባር ላይ ጣልቃ ሲገባ ቴስቶስቴሮን እና የወንድ የዘር ፍሬ ማምረት ይቀንሳል። በዚህ ምክንያት የወሲብ ፍላጎት ማጣት፣ ስንፈተ ወሲብ ወይም መሃንነት የመሳሰሉ ምልክቶችን ሊያስከትል ይችላል። በተጨማሪም ሃይለኛ ድካም፣ የጡንቻ ጥንካሬ ማጣት ያሳያል።

 

የፕሮላክቲኖማ አባጮች መጠን በጣም ትላልቅ ደረጃ ሲደርስ በዙሪያው ባሉ የአንጎል ሕብረ ሕዋሳት ላይ ጫናና መጨናነቅ ያስከትላል። በወንዶችም በሴቶችም ላይ ከፍተኛ ራስ ምታት ያመጣል። እብጠቱ በጣም ካደገ ደግሞ በአካባቢው ያሉ በአይን ነርቭን በመጫን የእይታ ችግርን ይፈጥራል። በተለይም የዳርቻ (የጎን) እይታን ሊጎዳ ይችላል። እየባሰ ሲሄድ በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ የአይን ብርሃን ማሳጣት ያስከትላል። በተጨማሪም የሌሎች ሆርሞኖች ማነስ ሊያስከትል ይችላል። 


ይህ በሽታ ሊያጋጥም እንደሚችል ለማወቅ ሰዎች ማድረግ ያለባቸው ነገር?

 

ፕሮላክቲኖማ ጾታ ሳይለይ በወንድ እና በሴት ላይ ይከሰታል። በአብዛኛው መካከለኛ የእድሜ ክልል ባሉ ሰዎች በተለይም ከ50 አመት በታች ነው የሚታየው።

 

በሰውነት ላይ ስለሚኖሩ ለውጦች መከታተልና ማወቅ ሁል ጊዜ ጠቃሚ ነው። ያልተለመደና ትክክል ያልመሰለን ስሜት ካለ ምንጊዜም ዶክተር ጋር ሄዶ ስለሚያስጨንቀን ነገር መወያየት ጥሩ ነው። የሆርሞን ህመም ሳይባባስ ቀደም ብሎ መመርመር ትልቅ ለውጥ ያመጣል። 


ለሴቶች የወር አበባ ዑደት እና ያልተጠበቁ የጡት ለውጦችን መከታተል ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። ወንዶች ያልተለመደ የድካም ስሜት ካጋጠማቸው ወይም የወሲብ ፍላጎት መቀነስ ካለ መታየት ይሻላል። ሁሌም ራስ ምታት ወይም የእይታ ለውጦች በፍፁም ቸል ሊባሉ አይገባም።


ፕሮላክቲኖማ እንዴት ይመረመራል?

 

አንድ ሰው ከላይ የጠቀስናቸው ምልክቶች ካጋጠመው የፕሮላኪኖማ ህመም ይሁን አይሁን ለማረጋገጥ አንዳንድ ቀላል ምርመራዎችን በማድረግ ማወቅ ይቻላል። በመጀመሪያ ደረጃ በደም ምርመራ አማካኝነት የፕሮላክቲንን መጠን ይመረመራል።


የፕሮላክቲን መጠን ከፍ ያለ ከሆነ ኤምአርአይ ምርመራ (MRI) ይታዘዛል። ይህም የእብጠቱን መጠን እና ትክክለኛ ቦታ ለማየት ይረዳል።


ፕሮላክቲኖማ እንዴት ይታከማል?

 

ጥሩ ዜናው ፕሮላክቲኖማ በጣም ታክሞ ሊድን የሚችል ነው። አብዛኛዎቹ የፕሮላክቲኖማ አይነቶች በመድሃኒት ይታከማሉ።


መድሃኒቶቹ የፕሮላክቲን መጠንን በከፍተኛ ሁኔታ ይቀንሳሉ፣ ወደ መደበኛ መጠን ያስተካክላሉ። በተጨማሪም የፕሮላክቲኖማ እባጩን መጠን ይቀንሳሉ። አብዛኛዎቹ ታካሚዎች ለዚህ የመድሃኒት ህክምና ጥሩ ውጤት ያሳያሉ። ሁሉም የህመም ምልክቶች ብዙውን ጊዜ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ይጠፋሉ።


ለአንዳንድ ሰዎች መድሃኒቶች ካልሰሩ ወይም መድሃኒቶች የጎንዮሽ ጉዳት ካመጡ እባጩን ለማስወገድ ኦፕሬሽን ሊደረግ ይችላል። ይህ የፒቱታሪ ኦፕሬሽን ብዙውን ጊዜ የሚከናወነው ረቀቅ ባለ መንገድ የራስ ቅል መከፈት ሳያስፈልግ በአፍንጫ በኩል በሚገባ ቀጭን መሳሪያ ነው። 


የፕሮላክቲኖማ ህክምና የረጅም ጊዜ ውጤቱ እንዴት ነው?

 

ፕሮላክቲኖማ በጊዜ ከታወቀ በቀላሉ ሊታከም የሚችል ሁኔታ ነው። ጥሩ ህክምና ማግኘት ከተቻለ መዳን የሚችል ነው። ህመሙ ከዳነም በኋላ የፕሮላክቲን መጠንን መከታተል እና እብጠቱ ተመልሶ እንዳያድግ ለማረጋገጥ መደበኛ ክትትል አስፈላጊ ነው።


ማስታወሻ፦ በዚህ መጣጥፍ ላይ የተካተቱት ይዘቶች ወይም ሀሳቦች ለአጠቃላይ መረጃ ብቻ ናቸው። ለግል ምርመራ ወይም ህክምና የጤና ባለሙያዎን ያማክሩ።


ተጨማሪ ምክር፣ እርምት ወይም ግብረ መልስ ለመስጠት በኢሜል፦ contact@melakutaye.com እና ስልክ፦ +251921720381 ማግኘት ይችላሉ። ለግል ህክምና ዶ/ር መላኩ ወይም የስራ ባልደረቦቹ ጋር በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የስኳር ህክምና ክፍል መመካከር ይችላሉ።


የተጣራና ታማኝ የጤና መረጃ ለሁሉም ኢትዮጵያዊያን ለማዳረስ እንዲረዳኝ በድህረ ገጽና ማህበራዊ ሚዲያ ገጾች ያሉ መረጃዎችን በማጋራት እና በመጋበዝ እንዲተባበሩ በትህትና እጠይቃለሁ።

ቴሌግራም https://t.me/hakimmelaku

Tiktok https://www.tiktok.com/@hakimmelaku

#Quality-Health-Information-For-All

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top