የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገሮች ውስጥ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ያጠቃል። በተለይም የእናቶችና ህጻናት የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ከፍተኛ ተጋላጭ ናቸው። እንደ ብረት፣ ዚንክ እና ቫይታሚን ያሉ ለጤና አስፈላጊ ንጥረ ነገሮች እጥረት ከሲሶ እስከ ግማሽ ያክሉን የማህበረሰብ ክፍል የሚያጠቃ ሥር የሰደደ ድብቅ ረሃብ ነው። የእነዚህ የቪታሚኖች እና ማዕድናት እጥረት የአካል እና የአእምሮ እድገት አቅም ይጎዳል።
ምግቦችን ማበልፀግ (food fortification) ሲባል በምግብ ዝግጅት እና ማሸግ ወቅት ምግቦች ላይ ቪታሚኖችን እና ማዕድኖችን በመጨመር የምግብነት ይዘታቸው ላይ እሴት ለመጨመር የሚደረግ ሂደት ነው። ይህ ተዘውትረው የሚበሉ ዋነኛ ምግቦችን ማበልፀግ ተግባር የምግብ እጥረትን ለመከላከል አንዱ ዉጤታማ ስትራቴጂ ነው። ምግብን ለማሻሻል እና የምግብ እጥረቶችን ለመከላከል አስተማማኝ ዘዴ ሲሆን በርካታ የጤና፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጠቀሜታዎች አሉት።
የምግብ ማበልጸግ ሂደትና ህግ እንደየሃገሩ ሁኔታዎች ላይ ተመሰረቶ የተለያዬ ሲሆን ለምሳሌም በዚያ ሃገር ያለው አመጋገብ ስርአትና ልምድ፣ የምግብ እጥረት አይነቶች ስፋት፣ የምግብ ማቀነባበሪያ አይነቶች እና መሠረተ ልማት ላይ መሰረት አድርጎ የተለያየ የምግብ ማበልጸግ ህጎች አሉ።
አንዳንድ ሃገሮች በኢንዱስትሪ ደረጃ መጠነ ሰፊ የሆነ የምግብ ማበልጸግ ሂደት በመከተል በብዛት ጥቅም ላይ የሚውሉ ምግቦችን በሙሉ ለምሳሌ እንደ ጨው፣ ዱቄት፣ ዘይት፣ ስኳር እና ሌሎችም ማጣፈጫዎች ሁሉ እንዲበለጽጉ አስገዳጅ (Mandatory fortification) ብሄራዊ ህግ አላቸው። ሌሎች ደግሞ ላላ ያለ በአምራቹ ፍቃደኝነት የምግብ ምርታቸውን በራሳቸው ፍቃድ (voluntary fortification) የሚያበለጽጉበት አሰራር አላቸው።
በምግብ ማቀነባበርና ማሸግ ወቅት ንጥረ-ምግቦች ከሚጨመሩበት ሂደት በተጨማሪ የምግብ ሰብሎች በሚበቅሉበትና በሚያድጉበት ወቅትም ማበልጸጊያ መንገዶች (biofortification) አሉ። ይህም ማለት ሰብል የሚበቅልበት አፈር እንዲሻሻል በማድረግ ወይም የእህል ማዳበሪያን በንጥረ-ምግቦች አጠናክሮ በመጨመር ሊሆን ይችላል።
አንዳንዴም በቤት ውስጥ በበሰለ እና ለመብላት በተዘጋጀው ምግብ ላይ ቫይታሚኖች እና ማዕድናት መጨመር (Point-of-Use / Home Fortification) የሚቻልበት ሁኔታ አለ። ለዚህ የሚረዱን በትንሹ እንደቅመም ታሽገው የሚዘጋጁ የንጥረ ምግብ ዱቄት (micronutrient powders) ምግባችን ማእድ ላይ ጣል በማድረግ ማጠናከር እንችላለን።
በኢትዮጵያ በህግ አስገዳጅነት እንዲበለጽጉ የተደረጉ የምግብ ምርቶች የሚከተሉት ናቸው።
1️⃣ የምግብ ጨው በአዮዲን የበለጸገ መሆን አለበት።
2️⃣ የምግብ ዘይት በቫይታሚን ኤ እና ቫይታሚን ዲ የበለጸገ መሆን አለበት።
3️⃣ የስንዴ ዱቄት በቫይታሚን ቢ እና ዚንክ የበለጸገ መሆን አለበት።
እነዚህን ምግቦች አምራቾች አበልጽገዉ ምርታቸዉ ላይ ‘የበለፀገ fortified’ የሚል ሎጎ መለጠፍ ግዴታ አለባቸው።
በመሆኑም እነዚህን በአስገዳጅነት እንዲበለፅጉ የተመረጡ ምግቦች ሲገዙ የበለፀገ ምግብ ምልክት የለጠፉ መሆናቸውን ልብ ይበሉ።
ለተጨማሪ መረጃ የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን ድህረ ገጽና ማህበራዊ ሚዲያ ገጾች ይጎብኙ።
ስለአዮዲን ምግብ አስፈላጊነት በዚህ ቪዲዮ ተጨማሪ ይመልከቱ።
ማስታወሻ፡ በዚህ ጽሁፍ የተካተቱት ይዘቶች ለአጠቃላይ መረጃ ብቻ ናቸው። ለግል ምርመራ ወይም ህክምና የጤና ባለሙያዎን ያማክሩ።
ይህ መረጃ ጠቃሚ ሆኖ እንዳገኙት ተስፋ አደርጋለሁ! ተጨማሪ ጥያቄዎች ካሉዎት የዚህን መረጃ ያሰናዳዉን ዶ/ር መላኩ ታዬ እና የስራ ባልደረቦቹን በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የስኳር ህክምና ክፍል ማግኘት ይችላሉ።