በአለም አቀፍ እንዲሁም በኢትዮጵያ ደረጃ የስኳር ህመም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ መጥቷል። በስኳር ህመም ዙርያ የሚነገሩ የተሳሳቱ አመለካከቶችና አሳች ፈዋሾችም እንዲሁ እንደወረርሽኝ በስፋት ይታዩ ጀምረዋል። የስኳር በሽታን ለማዳን የሚሰጡ የባህል ህክምና ምርቶች እዚህም እዚያም ይሰማሉ። ይባስ ብሎም ብዙ ታዳሚ ያላቸው ጋዜጦችና ቴሌቪዥን ሚዲያ ተቋማት ሳይንሳዊ ማስረጃ የሌላቸው ጎጂ አፈ ታሪኮች እና የተሳሳቱ አመለካከቶች ማሰራጫና ነጻ ማስተዋወቂያ መድረኮች ሆነዋል።
እነዚህ አሳች ፈዋሾች ብዙ ሰሚ ጆሮና ፈውስ ፈላጊ የሚያገኙበት ምስጢር ዘርፈ ብዙ ቢሆንም አንዱ ምክንያት በማህበረሰቡ ዘንድ ስለስኳር ህመም የግንዛቤ እጥረት መኖሩ ነው። ብዙውን ጊዜ በማህበረሰብ አእምሮ ውስጥ የሚታመኑ ተረት ተረቶችና አፈ ታሪኮች ላይ በመመስረት አንዳንዴም ትንሽ እውነት አዘል መረጃ በማሰራጨት ነው ቢዝነስ የሚሰሩት።
በእርግጥስ እነዚህ ‘ፈውስ’ የሚባሉት ይሠራሉን? መልሱ ብዙውን ጊዜ አይሆንም ነው።
በሻይ፣ በቡና፣ በቅመማ ቅመም፣ በስራስር፣ እና በሌሎችም መልክ ስለሚወሰዱ የስኳር “ፈውስ” ስለሚባሉት መረጃዎች በየቀኑ ብዙ የዋሆች ይታለላሉ። “ይህችን ቅመም አንድ ማንኪያ ለብ ባለ ውሃ በባዶ ሆድ ብትወስድ፤ ይህችን ሻይ ወደ ጸሃይ መውጫ ዞረህ በአንድ ትንፋሽ ብትጠጣ” ወዘተ የሚሉ መረጃዎች ይናፈሳሉ፤ አንዳንዴም በምናከብራቸው ጓደኞች ወይም የቤተሰብ አባላት የሚበረታታ ሊሆን ይችላል።
ብዙ የስኳር ህመም ያለባቸው ሰዎች ስለ አመጋገብ፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ፣ መድሃኒቶች እና የግሉኮስ ክትትል የሚሰጠው መልከ ብዙ የህክምና ምክር ፈጣን ውጤት ባለማግኘታቸው ወይም ግራ የሚያጋባ እርስ በርስ የሚጣረሱ ምክረ ሃሳቦች ‘’አቋራጭ ፈውስ’’ እንሰጣለን ለሚሉ አሳች ፈዋሾች ይጋለጣሉ።
አንዲህ አይነት አቋራጭ ፈውስ ፍለጋ በማንኛውም የሕክምና ማስረጃ እስካሁን አልተደገፈም። አንድ ምርት የስኳር በሽታን ይፈውሳል የሚለው ማንኛውም የይገባኛል ጥያቄ ውሸት ነው። እንደ እውነቱ ከሆነ ለስኳር ህመም አስካሁን አንዴ ብቻ ተወግቶ ወይም ተግቶ በዘላቂነት የሚያስታግስ ምንም ፈውስ አልተገኘም።
የአይነት አንድ የስኳር ህመምን (Type 1 diabetes) ለማዘግየት ተስፋ ሰጭ ውጤቶች እየታዩ ነው። ለምሳሌ በቅርቡ በተደረገ ጥናት Teplizumab የተባለ መድሃኒት የአይነት አንድ የስኳር ህመም ከፍተኛ ተጋላጭ ሰዎች ላይ ተሞክሮ ስኳር ከፍ ማለትን በሁለት አመት ያክል አዘግይቷል። ከዚህ ያለፈ ስኳርን ከነአካቴው ማጥፋት የቻለ መድሃኒት የለም – ለአይነት አንድ የስኳር ህመም።
የአይነት ሁለት ስኳርም (Type 2 diabetes) ቢሆን በአሁኑ ጊዜ ዘላቂ ስርየት የሚሰጥ ምንም ዓይነት መድኃኒት በአለም ላይ የለም። ይህ ማለት ምንም ተስፋ የለውም ማለት ግን አይደለም። ከፍተኛ ክብደት መቀነስና ቦርጭ በዘላቂነት ማጥፋት የሚችሉ በተወሰኑ ሰዎች በተለይም ስኳሩ ስር ያልሰደደ እና እድሜያቸው ያልገፋ ከፍተኛ የስኳር መሻሻል ያመጣል፤ መድሃኒት እንዲቀነስ ብሎም እንዲቆም ሊደረግ ይችላል (diabetes remission)። ይህ ደረጃ ግን ዘላቂ ላይሆን ይችላል። ስኳሩ ድጋሜ የመመለስ እድሉ ከፍተኛ ስለሆነም ተፈውሻለሁ ብሎ መዘናጋት ተገቢ አይደለም።
የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለስልጣን እና ሌሎችም የሚመለከታቸው ተቋማት የስኳር ሕክምናዎች በሳይንስ የተረጋገጡ፣ ደህንነታቸው የተጠበቀ እና ውጤታማ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ጥብቅ ቁጥጥር የሚያደርግ ቢሆንም የተሳሳቱ መረጃዎችን መለየት ብዙውን ጊዜ የእያንዳንዳችን ሃላፊነት ነው።
‘የስኳር ህመምን ይፈውሳሉ’ ውሸቶች እንዴት መለየት ይቻላል?
- ሁሉንም አይነት በሽታ ‘’ለመፈወስ፣ ለማከም ወይም ለመከላከል ይረዳል” ተብሎ የሚቀርብ ማንኛውም ለማመን የሚከብድ ወሬ (too good to be true) ውሸት የመሆን እድሉ ከፍተኛ ነው። አንድ ሰው በአንድ ቅጠል “ፈጣን የህመም ማስታገሻ”፣ “ፈጣን ክብደት መቀነስ” ወይም “የተረጋገጠ የደም ስኳር ማረጋጊያ” እሰጣለሁ ካለ እውነት አይደለም ማለት ነው። እነዚህ የእፈውሳለሁ ማደናገሪያዎች እምብዛም በሳይንሳዊ ማስረጃ አይደገፉም።
- አጠራጣሪ ቃላት መጠቀም ለምሳሌ “ሁሉም ተፈጥሯዊ”፣ “ተአምራዊ ፈውስ”፣ “ፈጣን እና ህመም የሌለበት ፈውስ”፣ ‘ምንም የጎንዮሽ ጉዳት የሌለው’ ወዘተ የሚል ቅስጥ ሃረጎች ካሉበት ተዓማኒነት ይጎለዋል።
- ከፊል ሳይንሳዊ የሚመስሉ ትርጉም የማይሰጡ ቃላትን ለምሳሌ ‘detoxification’ ከተጠቀሙም እውነት አይደለም ማለት ነው።
- የተቀመመ መድሃኒታቸው “ሚስጥራዊ ንጥረ ነገር” እንዳላቸውና ውህዱ እንዳይሰረቅብኝ በማለት ምን እንደሆነ ግልጽ ያልሆነ ፈውስ ካላቸውም መጠርጠር ይሻላል።
- ‘ብቻ’ የሚል ቅጥያ ካለውም ውሸት ነው ማለት ነው። ‘የኔ ቅመም ብቻ’፣ ‘የኔ ቅጠል ብቻ’ ነው ፈዋሽ ካሉ ችግር አለ ማለት ነው። ‘የእኔ የአመጋገብ ምክር ብቻ ነው ትክክል’ ካሉም ያው ነው። የስኳር ህመም መነሻው ዘርፈ ብዙ የሜታቦሊዝም መዛባት እንጅ አንድ ሰው ባለማወቅ ብቻ አመጋገብ ስላላስተካከለ በራሱ ላይ ያመጣው የስንፍና በሽታ አድርጎ መቁጠር ስህተት ነው።
- የሴራ ፅንሰ-ሀሳብ (conspiracy) የሚነዙ ከሆኑም እንዲሁ አሳች ናቸው ማለት ነው። ለምሳሌ መድሃኒት አምራቾችና ሃኪሞች ተመሳጥረው ነው ዋናውን የሚፈውሰውን መድሃኒት የደበቁት፤ ዶክተሮች በገንዘብ ተደልለው ነው የማያድን መድሃኒት ቀን በቀን እንድትወስድ የሚያደርጉህ ወዘተ ሊሆን ይችላል።
- የማይረጋገጡ የአድኖኛል ምስክርነቶች (witnesses) በአብዛኛው የተከፈላቸው ወይም በተለያየ መንገድ ተጠቃሚ የሆኑ ማስታዎቂያ የሚሰሩ ናቸው። የእኔ ህክምና መንገድ ይሰራል የሚል ካለ በሳይንሳዊ መንገድ ግልጽ አድርጎ ጥናታዊ ጽሁፍ ያሳትም ያስነብብ እንጅ ማንነታቸው ያልተረጋገጠ ጥቂት ሰዎችን ፊት ምስክርነት አሳይቶ ላሞኛችሁ ማለት ኋላቀር ኢ-ሳይንሳዊ አካሄድ ነው።
ማስታዎሻ፤ ለማመን የሚከብድ ወሬ (too good to be true) ውሸት የመሆን እድሉ ከፍተኛ ነው።
አንዲህ አይነት አሳች ፈዋሾችን ለመዋጋት የሚረዳን ትልቁ መሳሪያ እውቀት ነው። የተረጋገጡና ትክክለኛ የጤና መረጃን ተደራሽነት በማስፋት የተሳሳቱ አመለካከቶችን መቅረፍ ይቻላል።
ይህን ምክንያት በማደርግ ስኳርን ጨምሮ በበርካታ የጤና ጉዳዮች ዙርያ ግንዛቤን ለማስፋት የራሴን በጎ አስተዋጾ ለማድረግና አማራጭ የጤና መረጃ ምንጭ ይሆን ዘንድ በአዲስ የይዘትና አቀራረብ መንገድ ማህበራዊና መደበኛ ሚዲያዎች ላይ ለመስራት አስቤአለሁ።
የተጣራና ታማኝ የጤና መረጃ ለሁሉም ኢትዮጵያዊያን ለማዳረስ ጥረት ጀምሬያለሁ። ይህንን ጥረት ለብዙዎች ተደራሽ ይሆን ዘንድ በድህረ ገጽና ማህበራዊ ሚዲያ ገጾች ያሉ መረጃዎችን በማጋራት እና በመጋበዝ እንዲተባበሩ በትህትና እጠይቃለሁ።
ቴሌግራም https://t.me/hakimmelaku
Tiktok https://www.tiktok.com/@hakimmelaku
#Quality-Health-Information-For-All
ማስታወሻ፡ በዚህ ጽሁፍ የተካተቱት ይዘቶች ለአጠቃላይ መረጃ ብቻ ናቸው። ለግል ምርመራ ወይም ህክምና የጤና ባለሙያዎን ያማክሩ።
ተጨማሪ ጥያቄዎች ካሉዎት የዚህን መረጃ ያሰናዳዉን ዶ/ር መላኩ ታዬ በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የስኳር ህክምና ክፍል ማግኘት ይችላሉ።