በዶ/ር መላኩ ታዬ
በደም ውስጥ የሚገኙትን የኮሌስትሮል እና ትራይግሊሪይድ መጠን የሚለኩ ምርመራዎች የልብና የደም ስር ጤናን ለመለካት ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ። ይህ ምርመራ በተለምዶ በባዶ ሆድ ብቻ ነው የሚሰራው የሚል ልማድ አለ። በተለይም አንዳንድ የጤና ባለሙያዎች ረፋድ 3 ሰአት አካባቢ ካለፈ የኮሌስትሮል ምርመራ ‘አይሰራም፤ አልሰራም’ ብለው ተገልጋዩንም ምርመራውን ያዘዘውን ባለሙያም ሲያመናጭቁ አስተውያለሁ።
ልክ ነው በቀደመው የህክምና ዘመን ትክክለኛ የኮሌስትሮል መጠን ለመለካት በባዶ ሆድ ከ12 ሰአት በላይ ሳይበላ መሆን አለበት ይሉ ነበር። ነገር ግን ይህ አባባል በሳይንሳዊ ማስረጃ የተደገፈ ስላልነበር ተሽሯል። የቅርብ ጊዜ ጥናቶች ያረጋገጡት እና አለምአቀፍ የኮሌስትሮል ህክምና መመሪያዎች የሚመክሩት የኮሌስትሮል ምርመራ ለማሰራት መጾም ግዴታ እንዳልሆነ ነው።
የኮሌስትሮል ምርመራ ለማሰራት መጾም የግድ አስፈላጊ አለመሆኑን የሚያሳምኑ በርካታ ምክንያቶች አሉ።
- በማንኛውም ሰአት መጾም ሳያስፈልግ የሚሰራ የኮሌስትሮል ምርመራ (non fasting lipid profile) በበርካታ ሳይንሳዊ ጥናቶች የተደገፈ ነው። አለም አቀፍ የኮሌስትሮል ህክምና መመሪያዎች ለአብነትም የአሜሪካ ካርዲዮሎጂ ኮሌጅ (ACC)፣ የአሜሪካ የልብ ማህበር (AHA) እና የአውሮፓ አተሮስክለሮሲስ ማህበር (EAS) እና ሌሎችም መመሪያዎች ሁሉም ለአብዛኛዎቹ ሰዎች የኮሌስትሮል ምርመራ ለማሰራት የግድ በባዶ ሆድ መሆን አንደሌለባቸው ይጠቅሳሉ። በርካታ ጥናቶች እንደሚያሳዩት በጾም እና ሳይጾም የሚሰራ የኮሌስትሮል ምርመራ ውጤቶች መካከል ያለው ልዩነት እጅግ በጣም አነስተኛ ነው። ትንሽ ልዩነት ቢኖር እንኳ እጅግ ኢምንት ስለሆነ የህክምና ውሳኔ ላይ ምንም ተጽዕኖ አያሳድርም።
- እንዲያውም በባዶ ሆድ ብቻ የሚሰራ የኮሌስትሮል ምርመራ እውነተኛ ህይወታችንን አያንጸባርቅም። ለምን ቢሉ ሰውነታችን በቀን ውስጥ አብዛኛውን ጊዜ እየጾመ አይደለማ! ሰውነታችን በአብዛኛው ህይወታችንን የሚፈጀው ፆም ባልሆነ ሁኔታ ውስጥ ነው (ይህ ሲባል ማእድ አቅርበን የምንበላበትን ጊዜ ብቻ ሳይሆን የበላነው ምግብ ሲፈጭ፣ ሲንሸራሸር፣ ሲዋሃድ፣ ሲቃጠል፣ ሲወገድ ወዘተ ለማለት ነው)። ስለሆነም በጾም ብቻ የሚሰራ የኮሌስትሮል ምርመራ እውነተኛውን የሰውነታችንን ሜታቦሊዝም አያሳይም። ሳይጾም የሚሰራ የኮሌስትሮል ምርመራ የደም ቅባት (lipid) ሜታቦሊዝምን የተሻለ ትክክለኛ ገጽታ ይናገራል።
- ሌላው በጾም ብቻ የሚባል ምርመራ ለታካሚው ምቹ አይደለም። ይልቁንም ታካሚው ወደጤና ተቋም በመጣበት አጋጣሚ ሁሉ ምርመራ ማድረጉ የተሻለ ሂደቱን ቀላል ያደርገዋል። የኮሌስትሮል ምርመራ ለማሰራት በሌሊት ተነስተህ ላብራቶሪ በር በማለዳው ድረስ ማለት ለብዙ ሰው አይመችም። ከቤት ሲወጣ መድሃኒት መውሰድ ያለበት ካለም እንዲሁ መድሃኒቱን እንዲያቆራርጥ እያስገደድነው ይሆናል። በነዚህ ምክንያቶች ብዙ ሰው ምርመራ ከማድረግ ወደኋላ ይላል። በተቃራኒው በማንኛውም ሰአት የሚሰራ የኮሌስትሮል ምርመራ ምቹና ቀላል ነው። ብዙ ሰዎች ምርመራ እንዲያደርጉ ያበረታታል። ስለ ምቾት ብቻም አይደለም፤ ሳይንሳዊም ነው።
የኮሌስትሮል ምርምራ በጾም ብቻ እንዲሰራ የሚያስገድዱ በጣም አልፎ አልፎ የሚከሰቱ በዘረ መል ችግር የሚመጡ የኮሌስትሮል ህመም አይነቶች አሉ። መጾም የሚመከርባቸው ልዩ ሁኔታዎች የሚባሉት እጅግ በጣም ከፍተኛ ትራይግሊሰርይድ (hypertriglyceridemia > 400 ሚሊ ግራም በላይ) ታካሚዎች ላይ ብቻ ነው። ይሁን እንጂ እነዚህ ጉዳዮች ከጠቅላላው ኮሌስትሮም ምርመራ ከሚያስፈልጋቸው ሰዎች በጣም ትንሽ ፐርሰንት ብቻ የሚወክሉ ናቸው።
ማንኛውም ሰው ወደጤና ተቋም ሲመጣ የኮሌስትሮል ምርመራ ካስፈለገው ወዲያውኑ በመስራት የልብና የደም ስር ጤና ደረጃቸውን እንዲረዱ እና ተገቢውን ምላሽ እንዲተገብሩ በማገዝ እንተባበር እንጅ በጠዋት ተመለስ ብለን ወርቃማ እድል አናባክን።
ስለዚህ በባዶ ሆድ ካልሆነ የኮሌስትሮል ምርመራ አልሰራም የሚል ባለሙያ ካለ አሰራሩን ያዘምን። የተሻሻሉ የህክምና መመሪያዎችን በመላመድ የጤና እንክብካቤን የበለጠ ተደራሽ፣ ውጤታማ እና ታካሚን ማዕከል ያደረገ እንዲሆን ማድረግና ምቹ አገልግሎት ለመስጠት ጊዜው አሁን ነው።
ማስታወሻ፡ በዚህ ጽሁፍ የተካተቱት ይዘቶች ለአጠቃላይ መረጃ ብቻ ናቸው። ለግል ምርመራ ወይም ህክምና የጤና ባለሙያዎን ያማክሩ።
ይህ መረጃ ጠቃሚ ሆኖ እንዳገኙት ተስፋ አደርጋለሁ! ተጨማሪ ጥያቄዎች ካሉዎት የዚህን መረጃ ያሰናዳዉን ዶ/ር መላኩ ታዬ እና የስራ ባልደረቦቹን በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የስኳር ህክምና ክፍል ማግኘት ይችላሉ። ውድ የሆነውን ጤናዎትን ለመጠበቅ ምን ማድረግ እንዳለብዎት ለማዎቅ ተጨማሪ ተግባራዊ ምክሮችን በዶ/ር መላኩ ድህረ ገጽ www.melakutaye.com እና ማህበራዊ ሚዲያዎች @hakimmelaku ይከታተሉ!