ከወሊድ በኋላ የሚደረግ የስኳር ክትትል

የእርግዝና ወቅት ስኳር ህመም የተገኘባቸው ብዙ እናቶች ከወሊድ በኋላ እርግፍ አድረገው ይረሱታል። ‘ዶክተሬ ከወሊድ በኋላ ስኳር ይስተካከላል ስላለኝ ተውኩት’ የሚል ንግግር መስማት የተለመደ ነው። አራስ ልጅ መያዝና መንከባከብ በራሱ በጣም አድካሚ ስራ ስለሆነ ብዙ እናቶች ስለራሳቸው ጤና ለማሰብ ጊዜም አያገኙ።


ማስተዋል ያለብን ነገር ቢኖር የእርግዝና ጊዜ ስኳር ክትትል ከወሊድ በኋላ አያበቃም። የእርግዝና ጊዜ ስኳር የተገኘባት ሴት የስኳር ክትትል ከወሊድ በኋላም መቀጠል አለባት። የድህረ-ወሊድ የስኳር ምርመራ በእርግዝና ጊዜ እንደሚደረገው ህክምና ሁሉ የእናቷን ጤና ለመጠበቅ ወሳኝ ነው።


ከወሊድ በኋላ ስኳር ምርመራ ለምን አስፈለገ?

በእርግዝና ወቅት የሚከሰት የስኳር ህመም የሚከስተው ከእንግዴ ልጁ የሚመነጩ ስኳር አምጭ ሆርሞኖች ምክንያት ነው። ይህ የሚከሰተው ከአምስት እናቶች አንዷ ላይ ሲሆን የቀሩት 80 በመቶ እናቶች የሆርሞኖችን ጫና በመቋቋም የደም ስኳር በመደበኛ ክልል ውስጥ ይቆጣጠራሉ። ይህ ማለት 20 በመቶ ነፍሰ ጡር እናቶች ቆሽታቸው የእርግዝና ሆርሞን ጫናን/ፈተናን መቋቋም አልቻለም ማለት ነው። ምንም እንኳን ከወሊድ በኋላ የደም ስኳር ወደ መደበኛው ቢመለስም ጂዲኤም መከሰቱ ሴቷ ወደፊት በዓይነት 2 የስኳር ህመም የመያዝ እድል ከፍ ያለ ይሆናል ማለት ነው።


የእርግዝና ወቅት ጊዜያዊ የስኳር ህመም ለዓይነት 2 የስኳር በሽታ ተጋላጭነት እንዴት ይጨምራል የሚለውን ሃሳብ ለማብራራት በምሳሌ ለማስረዳት ልሞክር።


ቆሽታችንን ኢንሱሊን እንደሚያመርት ፋብሪካ እናስበው። እንደሚታወቀው ኢንሱሊን የደም ስኳር (ግሉኮስ) ወደሃይልነት እንዲቃጠል የሚረዳ ሆርሞን ነው። ቆሽት በትክክል ከሰራ ተመጣጣኝ ኢንሱሊን በማምረት የደም ስኳር መጠን ሚዛንን በተገቢው ሁኔታ ይጠብቃል። የሸማች ፍላጎት ሲጨምር ፋብሪካም ምርት እንደሚጨምረው ሁሉ ቆሽትም በእርግዝና ምክንያት የሚመጣውን ድንገተኛ የሆርሞን ጫና ለመቋቋም የኢንሱሊን ምርት መጨመር አለበት። ቆሽት ጤነኛ ከሆነ በተቀላጠፈ ሁኔታ የኢንሱሊን ምርት ከፍ አድርጎ በእርግዝናው ምክንያት የጨመረውን የኢንሱሊን ምርት ፍላጎት ያሟላል። በዚህም የደም ስኳር በመደበኛ መጠን ውስጥ ይቆጣጠራል። ነገር ግን የኢንሱሊን ምርት መጨመር ሂደት በበቂ ደረጃ ፍላጎቱን ካላሟላ የደም ስኳር መጠን መጨመር ይጀምራል፤ የእርግዝና ወቅት ስኳር ይከሰታል ማለት ነው።


ቆሽት የእርግዝና ፈተናውን መቋቋም ይችላል ወስይ አይችልም ነው ጥያቄው። በእርግዝና ወቅት ሰውነት በድንገት ተጨማሪ ኢንሱሊን ይፈልጋል። ይህን ፍላጎት ለማሟላት ቆሽት ተጨማሪ ስራ መስራት አለበት። ፍላጎቱን ማሟላት ካልቻለ የደም ስኳር መጠን ይጨምራል። ከወሊድ በኋላም ቢሆን ፈተና ካበዛንበት (ክብደት ከጨመርን፣ ምግብ አላግባብ ከሆነ፣ ስፖርት ካላዘወተርን፣ ጭንቀት ካበዛን፣ ስኳር አምጭ መድሃኒት ከወሰድን ወዘተ) ቆሽት መቋቋም እንደማይችል አመላካች ነው። ስለሆነም በቀላሉ ወደ 2 ዓይነት የስኳር ህመም ይመራል።


በእርግዝና ወቅት ስኳር መታየቱ ቆሽቱ ወደፊት የሚገጥሙትን ሜታቦሊክ ፈተናዎች መቋቋም እንደማይችል ማሳያ ምልክት ነው። ቆሽት በእርግዝና ወቅት ፈተናውን መቋቋም ካልቻለ በኋለኛው ህይወታችን ውስጥ የሚመጡ ሜታቦሊክ ጫናዎችን ያለማለፍ ዕድሉ ከፍ ያለ ነው።


አለም አቀፍ ጥናቶችና ተሞክሮዎች እንደሚያሳዩት አስቀድመው በመመርመር አስፈላጊውን ቅድመ ጥንቃቄ እና ማስተካከያ እርምጃ ካልወሰዱ በእርግዝና ጊዜ ስኳር የታየባቸው ሴቶች መካከል ግማሽ ያህሉ ከእርግዝናው በኋላ ከ5 እስከ 10 ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ ዓይነት 2 የስኳር ህመም ይጠቃሉ።


የድህረ ወሊድ የስኳር ምርመራ

የወደፊት ስኳር የመያዝ እድልም ለመቀነስ እና አስቀድሞ ለመከላከል አንደኛው ቁልፍ እርምጃ መመርመር ነው።


ድህረ ወሊድ ከ6 እስከ 12 ሳምንታት ባለው ጊዜ ውስጥ እንደገና የስኳር ምርመራ በማድረግ ስኳሩ መስተካከሉን ማረጋገጥ ይገባል። ከዚያም በኋላ የስኳር ቅድመ ምርመራዎችዎን ቢያንስ በየሶስት አመቱ መመርመር ያስፈልጋታል።


ቅድመ ስኳር ደረጃ ከተገኘ ቋሚ ክትትል እና የአኗኗር ዘይቤ ማስተካከያ ማድረግ ወደ ዓይነት 2 የስኳር ህመም ደረጃ እንዳይሄድ ይከላከላል።


ከጂዲኤም በኋላ የሚመጣ የስኳር ተጋላጭነት እንዴት መከላከል ይቻላል?

ከወሊድ በኋላ የሚኖርን የስኳር ህመም ተጋላጭነት ለመቀነስ የሚያስችሉ በርካታ መከላከያ መንገዶች አሉ። ለሁሉም ሴት የሚሆን አንድ የአኗኗር ዘይቤ ቀመር ማስቀመጥ ባይቻልም ዋና ዋና መርሆዎቹ የሚከተሉት ናቸው።


ዋነኛው ቁልፍ መከላከያ ጋሻችን ጤናማ እና የተመጣጠነ አመጋገብ ማዘውተር ነው። ይህ ሲባል የግድ በጣም ከባድ የሆነ የማያዛልቅ አመጋገብ ስታይል መከተል አያስፈልግም። ከፋብሪካ ከተቀነባበሩ ምግቦች ይልቅ በፋይበር የበለጸጉ አትክልት፣ ፍራፍሬ እና እህል ምግቦችን ይምረጡ። ፋይበር የወጣላቸው ቀላል ስኳር ምግቦች ይቀንሱ። ለስላሳ እና ጣሻጭ መጠጦችን/ምግቦችን ያስወግዱ። አልኮልና ሲጋራም አይጠቀሙ።


ሌላኛው የተስተካከለ አኗኗር ዘይቤ መሰረት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማዘውተር ነው። የግድ ጂም መግባት ባያስልፈልግም በተቻለው መጠን፣ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ተንቀሳቀሱ። በቀን ለ30 ደቂቃ የማያንስ ይንቀሳቀሱ፣ ከ10 ሺህ እርምጃ በላይ ይራመዱ። ከተቻለ በሳምንት ሁለት ወይ ሶስቴ የጥንካሬ ስፖርት ይስሩ። የሚያስደስትዎትን ማንኛውም እንቅስቃሴዎችን ለምሳሌ ዳንስ፣ ዋና፣ ዮጋ ወዘተ ያዘውትሩ።


ክብደትን መቆጣጠር ወሳኝ ነው። ከወሊድ በኋላ አመጋገብም እንቅስቃሴም ስለሚበላሽ ክብደት ማስተካከል ቀላል አይሆንም። ነገር ግን በንቃት ከተከታተልሽው ማስተካከል የሚቻል ነው።


ጡት የሚያጠቡ ሴቶች ለአይነት 2 የስኳር በሽታ የመጋለጥ እድላቸው ይቀንሳል። ጡት ማጥባት ስኳር መጠንን ለመቆጣጠር ስለሚረዳ ጡት ማጥባትን አስቢበት።


ቋሚ ክትትል ማድረግ አትርሺ!


ማጠቃለያ

ብዙ ሴቶች የልጃቸው እንክብካቤ ላይ ብቻ በማተኮር የራሳቸውን ጤና ችላ ማለት ይታይባቸዋል። ፋታ የማይሰጥ ልጅ የማሳደግ ሃላፊነት፣ ዳይፐር መቀየር፣ እንቅልፍ ማጣት ወዘተ የእናትነት ስራ ምክንያት ከወሊድ በኋላ የስኳር ምርመራ ማሰራት ይዘነጋሉ። የራስን ጤና መጠበቅ ቅድሚያ የምትሰጠው ጉዳይ አይሆንም። ነገር ግን የእናትን ጤና መጠበቅ የሙሉ ቤተሰቡን ደህንነት እንደመጠበቅ ነውና ትኩረት ያሻዋል።


ስለሆነም ጂዲኤም ከነበረብሽ ዛሬዉኑ ከወሊድ በኋላ ለሚደረገው የስኳር ምርመራ ቀጠሮ ያዥ።


ጂዲኤም የነበረባት እናት የምታውቁ ከሆነ እንድትመረምር አስታውሷት።


የጤና ባለሟያም ከሆንክ/ሽ እያንዳንዱ እናት ከጂዲኤም በኋላ እንድትከታተል አበረታታ/ች።


አሁኑኑ የመከላከያ እርምጃ በመውሰድ የረዥም ጊዜ ጤናሽን ለመጠበቅ ተነሽ።


ማስታወሻ፦ በዚህ መጣጥፍ ላይ የተካተቱት ሀሳቦች ለአጠቃላይ መረጃ ብቻ ናቸው። ለግል ምርመራ ወይም ህክምና ዶ/ር መላኩ ጋር በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የስኳር ህክምና ክፍል ወይም የግል ሆስፒታሎች መመካከር ይችላሉ።


በመረጃ የተደገፉና የተረጋገጡ ተግባራዊ የጤና ምክሮችን በዶ/ር መላኩ Blog, Telegram, YouTube & Tiktok ይከታተሉ። እነዚህን የተረጋገጡ መረጃዎች ለሌሎችም እንዲያጋሩ በትህትና እጋብዛለሁ።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

Scroll to Top